ከ31 ሚሊየን ብር በላይ ግምት ያላቸው የኮንትሮባንድ እቃዎች ተያዙ

መጋቢት 4/2013 (ዋልታ) በአንድ ሳምንት ውስጥ ከ 31 ሚሊየን ብር በላይ ግምታዊ ዋጋ ያላቸው የኮንትሮባንድ እቃዎች መያዛቸው ተገለፀ፡፡

ግምታዊ ዋጋቸው 31 ሚሊየን 3 መቶ 94 ሺ 775 ብር የሆኑ እቃዎች በህገ ወጥ መንገድ ከሀገር ሊወጡና ወደ ሀገር ሊገቡ ሲሉ ከየካቲት 20 እስከ መጋቢት 2 /2013 ዓም ባሉት ቀናት በቁጥጥር ስር ውሏል ፡፡

ከተያዙት የኮንትሮባንድ እቃዎች 29 ሚሊየን 6 መቶ 75 ሺ 395 ብር ግምታዊ ዋጋ ያላቸው እቃዎች ወደ ሀገር ሊገቡ ሲሉ መያዘው ተጠቆመ፡፡

ቀሪዎቹ 1 ሚሊየን 7 መቶ 19 ሺ 380 ብር ግምታዊ ዋጋ ያላቸው እቃዎች ደግሞ ከሀገር ሊወጡ ሲሉ በተለያዩ የጉምሩክ ኬላዎች የተያዙ ናቸው፡፡

ከተያዙት የኮንትሮባንድ እቃዎች መካከል የተለያዩ ሀገራት ገንዘቦች፣ የጦር መሳሪያዎች፣ መድኃኒቶች፣ አደንዛዥ እፆች፣የቀንድ ከብቶች እና ምግብ ነክ ሸቀጣሸቀጦች፣ አልባሳትና ጫማዎች፣ የኤሌክትሮኒክስ እቃዎች፣ ኮስሞቲክስ፣ የመለዋወጫ እቃዎች ይገኙበታል፡፡

እቃዎቹ የተያዙት በጉምሩክ ስራተኞችና በፀጥታ አካላት ርብርብ እንዲሁም በህብረተሱ ተሳትፎ ነው ተብሏል፡፡

የኮንትሮባንድ እቃዎቹን ሲያጓጉዙ የነበሩ 32 ተሽከርካሪዎችና 3 ተጠርጣሪዎችም በቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡

ኮንትሮባድና ህገ ወጥ ንግድ የህዝብ ሰላምና ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥል፣ ህጋዊ የንግድ ስርዓቱን በማዛባት ፍትሃዊ ውድድር ሚጎዳና ገቢ በአግባቡ እንዳይሰበሰብና ሀገራችን ለልማት የሚያስፈልጋት ወጪ በታክስ ገቢ እንዳትሸፈን የሚያደርግ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል የሚጎዳ ህገ-ወጥ ተግባር ነው፡፡

ስለሆነም ይህንን የሰላም፣የጤና እና የልማት ጸር የሆነውን ኮንትሮባንድ በተባበረ ክንድ ሊከስም እንደሚገባ በገቢዎች ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያሳያል፡፡