አቶ ደመቀ መኮንን ከደቡብ ኮርያና ከጃፓን አምባሳደሮች ጋር ተወያዩ

አቶ ደመቀ መኮንን እና የደቡብ ኮሪያ አምባሳደር ካንግ ሲዮክ ሂ

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በኢትዮጵያ የደቡብ ኮሪያ እና ጃፓን አምባሳደሮችን በጽ/ቤታቸው ተቀብለው አነጋገሩ፡፡

አቶ ደመቀ ከደቡብ ኮሪያ አምባሳደር ካንግ ሲዮክ ሂ ጋር ባደረጉት ውይይት ኢትዮጵያ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል ለምታደርገው ጥረት ደቡብ ኮሪያ የቁሳቁስ ድጋፍ እንዲሁም የተሞክሮ ልውውጥ በማድረግ ላበረከተችው አስተዋጽአ የኢትዮጵያ ህዝብ እና መንግስት ያላቸውን አድናቆት ገልጸውላቸዋል።

ሚኒስትሩ ደቡብ ኮሪያ የምትከተለውን የልማት ሞዴል ኢትዮጵያ የምታደንቅ መሆኑንም ገልጸዋል።

አምባሳደር ካንግ ሲዮክሂ በበኩላቸው፣ በኮርያ ጦርነት ወቅት የኢትዮጵያ ወታደሮች ከደቡብ ኮርያ ጎን በመቆም ያደረጉትን አስተዋጽኦ በማውሳት፤ በሁለቱ አገራት መካከል ያለው ግንኙነት በደም የተሳሰረ ታሪካዊ ግንኙነት መሆኑን አንስተዋል።

በሁለቱ አገራት መካከል ያለው ታሪካዊ ግንኙነት በቴክኖሎጂ ሽግግር እና የልማት ፕሮጀክቶች ትብብር መስክ አሁን ካለው የሁለትዮሽ ትብብር ባሻገር የበለጠ ማጠናከር እንደሚያስፈለግ ጨምረው ገልጸዋል።

አቶ ደመቀ መኮንን እና የጃፓን አምባሳደር ኢቶ ታካኮ

በሌላ በኩል አቶ ደመቀ ከጃፓን አምባሳደር ኢቶ ታካኮ ጋር ባደረጉት ውይይት፣ በሁለቱ አገራት መካከል በትምህርት፣ በመሰረተ ልማት ግንባታ እንዲሁም በተሞክሮ ልውውጥ መስኮች ያለው ትብብር በየጊዜው እያደገ የመጣ ስለመሆኑ አንስተው፤ ለዚህም ያላቸውን አድናቆት ገልጸውላቸዋል።

ሚኒስትሩ አያይዘውም የጃፓን የልማት ትብብር ኤጀንሲ በአገራችን ስለሚያካሂዳቸው የልማት ድጋፍ ፕሮግራሞች ምስጋና አቅርበዋል።

በተጨማሪም በትግራይ ክልል እየተካሄደ ስላለው የሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦትና የመልሶ ግንባታ ስራዎችን በተመለከተ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን  ገለጻ ማድረጋቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡