ለምርጫው ሰላማዊነትና ዴሞክራሲያዊነት እየሰራሁ ነው – ኢዜማ

መጋቢት 12/2013 (ዋልታ) – 6ኛው ሀገራዊና ክልላዊ ምርጫ የኢትዮጵያ ህዝብ ልእልና የሚያረጋግጥበት አጋጣሚ በመሆኑ ምርጫው ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የበኩሉን እየተወጣ መሆኑን የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) አስታወቀ፡፡

ፓርቲው በጎንደር ከተማ ለአባላቱና ለደጋፊዎቹ እጩ ተወዳዳሪዎቹንና የመወዳደሪያ ምልክቱን ዛሬ አስተዋውቋል፡፡

የፓርቲው ምክትል ሊቀ-መንበር አቶ አንዱአለም አራጌ በመድረኩ ላይ እንደገለጹት ፓርቲው በመላ ሀገሪቱ በሚገኙ 448 ወረዳዎች የሚወዳደሩ እጩዎችን በዴሞክራሲያዊ መንገድ አስመርጦ አቅርቧል።

ፓርቲው በኢትዮጵያ ደረጃ 278 ቢሮዎችን ከፍቶ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ጠቅሰው ከዚህ ቀደም በመንግስት ደረጃ ያልተተገበሩ 42 ፖሊሲዎችን በፓርቲው አመራሮችና በምሁራን ተሳትፎ ማዘጋጀቱን ተናግረዋል፡፡

ፓርቲው በኮታና በብሄር በተውጣጣ አመራርና ባለሙያ ሳይሆን የእውቀት፣ የብቃት፣ የክህሎትና የታማኝነት መስፈርቶችን መሰረት ባደረገ መልኩ ሀገር የመምራት ተልእኮን በማንገብ ኢትዮጵያን ለመለወጥ ሰፊ ዝግጅት ማድረጉን ገልጸዋል፡፡

”ፓርቲው ስልጣን ላይ ከወጣ በኋላ ኢትዮጵያን የሙከራ ጣቢያ አያደርጋትም” ያሉት ምክትል ሊቀ-መንበሩ ”እየተሳሳትን ሳይሆን የምንማረው አስቀደምን ሀገር የምንመራበትን በሳል ፖሊሲዎችን አዘጋጅተን ነው” ብለዋል።

”ጎንደር የታሪክ ከፍታ ያላት ቀደምት ከተማ  መሆኗን አመልክተው ከተማዋ ዘመኑን በሚመጥን በተሻለ ከፍታ ላይ እንድትሆን ኢዜማ አበክሮ እንደሚሰራ አመላክተዋል፡፡

ምርጫው የኢትዮጵያ ህዝብ ልእልና የሚረጋገጥበትና ከአንድ ፓርቲ ማሸነፍ በላይ እንደሆነ ጠቁመው ሰላማዊና ዴሚክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ፓርቲው የበኩሉን ሃላፊነት እየተወጣ መሆኑን አስታውቀዋል።

ፓርቲው የመወዳደሪያ ምልክቱ ሚዛን መሆኑን በይፋ ያስተዋወቀ ሲሆን የእጩዎች ትውውቅም አካሂዷል፡፡

በመድረኩ ፓርቲው ለአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር በእጩነት ያቀረባቸው አቶ ክቡር ገናን ጨምሮ የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች መገኘታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡