ምርጫው ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲከናወን የድርሻቸውን እንደሚወጡ በመተከል ዞን የሚወዳደሩ የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች ገለጹ

መጋቢት 12/2013 (ዋልታ) – በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን 6ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መልኩ እንዲከናወን የበኩላቸውን ሚና እንደሚወጡ በዞን የሚወዳደሩ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች ገለጹ።

በዘንድሮው ምርጫ በዞኑ ብልጽግናን፣ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ)፣ የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ (አብን) እና የቦሮ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲን ወክለው የሚወዳደሩ አመራሮች አስተያየታቸውን ለኢዜአ ሰጥተዋል።

በዞኑ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ተፈጥሮ 6ኛው ጠቅላላ ምርጫ እስከ ፍፃሜው ስላማዊና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን የየድርሻቸውን እንደሚዎጡም አረጋግጠዋል።

የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄን በመወከል ለክልል ምክር ቤት የሚወዳደሩት አቶ አዲሱ ሲሳይ የእጩ ምዝገባው በሰለማዊ መንገድ መከናወኑን ገልጸው፣ በዞኑ ምርጫው ሰላማዊ፣ ፍትሃዊና  ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን የድርሻቸውን እንደሚወጡና ለስኬታማነቱ ሁሉም የድርሻውን መወጣት ይኖርበታልም ብለዋል።

ምርጫው ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ፓርቲያቸው ጠንካራ አቋም እንዳለውም ተናግረዋል።

በመተከል ዞን የቦሮ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ እጩ ተወዳዳሪ አቶ አርጋታ በላይ በበኩላቸው፣ የዘንድሮው ምርጫ በኢትዮጵያ ከዚህ በፊት ከተደረጉ ምርጫዎች በተሻለ መልኩ ዴሞክራሲያዊ፣ ተአማኒና ሁሉንም እኩል የሚያሳትፍ እንደሚሆን ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

ምርጫው ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን ፓርቲያቸው ለአባላቶቹና ደጋፍዎቹ ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ እያከናወነ መሆኑንም አረጋግጠዋል።

በዞኑ የኢዜማ ተወካይ አቶ ተመስገን አልቃ ምርጫው ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲካሄድ ፓርቲያቸው የድርሻውን በመወጣት ላይ መሆኑን ገልጸዋል።

የመተከል ዞን የብልፅግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ሙሉጌታ አንተነህ በበኩላቸው ጠቅላላ ምርጫው ሁሉንም አሳታፊ፣ ዴሞክራሲያዊና ሰላማዊ እንዲሆን ፓርቲያቸው እየሰራ መሆኑን አረጋግጠዋል።

ምርጫው ስኬታማ  እንዲሆን በዞኑ የሚንቀሳቀሱ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ካለው ወቅታዊ ሁኔታ አንፃር ችግር እንዳያጋጥማቸው ከባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።

የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮቹ በዞኑ የተቀናጀው ግብረ ሃይል ከተቋቋመ ወዲህ አንፃራዊ ሰላም መኖሩን ገልጸው፤ ምርጫው ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን በትብብር እንሰራለን ሲሉ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ባወጣው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫ ግንቦት 28 ቀን 2013 ዓ.ም የሚካሄድ ይሆናል።