ፕሬዚዳንት ጆን ፖምቤ ማጉፉሊ ሙስናን ለመከላከልና ጠንካራ የስራ ባሕል ለማዳበር ብርቱ ጥረት አድርገዋል – ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ

መጋቢት 13/2013 (ዋልታ) – የቀድሞው የታንዛኒያ ፕሬዚዳንት ጆን ፖምቤ ማጉፉሊ ሙስናን በመከላከል ጠንካራ የስራ ባህል እንዲዳብር ብርቱ ጥረት ማድረጋቸውን ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ገለጹ።
ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ በታንዛኒያው ፕሬዚዳንት ጆሴፍ ፖምቤ ማጉፉሊ ሞት የተሰማቸውን ሀዘን አዲስ አበባ በሚገኘው የአገሪቷ ኤምባሲ በመገኘት ገልጸዋል።
ፕሬዚዳንቷ ለታንዛኒያ ሕዝብ፣ መንግስትና ለፕሬዚዳንቱ ቤተሰቦች በኢትዮጵያ ሕዝብና መንግስት እንዲሁም በራሳቸው ስም ባስተላለፉት መልዕክት፣ ፕሬዚዳንት ማጉፉሊ ለአገራቸው ታንዛኒያ እድገትና ሠላም ለማምጣት ባደረጉት ጥረት ሲታወሱ እንደሚኖሩ ገልፀዋል።
ሙስናና ብልሹ አሰራርን በመከላከል እንዲሁም በዜጎች መካከል ጠንካራ የስራ ባሕል እንዲፈጠር ስላደረጉት ጥረትም እንዲሁ።
እንደ ኢዜአ ዘገባ ፕሬዚዳንት ማጉፉሊ የኢትዮጵያና የኢትዮጵያዊያን መልካም ወዳጅ ነበሩ ያሉት ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ፤ ከስድስት ሳምንታት በፊት ዳሬሰላም ላይ ሲያገኟቸው ሙሉ ጤነኛ እንደነበሩ አስታውሰዋል።
በወቅቱ የሁለቱን አገራት ትብብር ማሳደግ በሚቻልበት ሁኔታ ውጤታማ ውይይት አድርገን ነበርም ብለዋል።
ጆን ማጉፉሊ ለአገራቸውና ለአፍሪካ ጥልቅ ፍቅር ያላቸው ታላቅ መሪ በመሆናቸው ሁላችንም አጥተናቸዋል በዚህም ጥልቅ ሐዘን ተሰምቶናል ብለዋል ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ።
በኤምባሲው በመገኘት ባሰፈሩት የሐዘን መግለጫ የፕሬዚዳንት ማጉፉሊን መልካም ስብዕና፣ ለአገራቸው፣ ለአፍሪካም ሆነ ለሰው ልጆች የነበራቸው ክብር ሁሌም ሲያስታውሱ እንደሚኖሩ ጠቅሰዋል።
የታንዛኒያ ፕሬዚዳንት የነበሩት ጆን ፖምቤ ማጉፉሊ ባጋጠማቸው የልብ ሕመም ሳቢያ በዳሬሰላም ሆስፒታል በሕክምና ሲረዱ ቆይተው በ61 ዓመታቸው ባለፈው ሣምንት ሕይወታቸው ማለፉ ይታወሳል።
ጆን ማጉፉሊ የታንዛኒያ ፕሬዚዳንት ሆነው የተመረጡት በ56 ዓመታቸው እንደ አውሮፓዊያኑ የዘመን ቀመር በ2015 ነበር።