ቦርዱ የምርጫ ቁሳቁስ ስርጭትና እንቅስቃሴን በተመለከተ ለፖለቲካ ፓርቲዎች ገለፃ አደረገ

ሚያዝያ 06/2013 (ዋልታ) – የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የምርጫ ቁሳቁስ ስርጭትና እንቅስቃሴን በተመለከተ ለፖለቲካ ፓርቲዎች ገለፃ አድርጓል፡፡
በ674 የምርጫ ክልሎች ለ50 ሺህ የምርጫ ጣቢያዎች የመራጮች ቁሳቁስ ስርጭት ለማድረግ በየክልሉ በቂ የትራንስፖርት ማህበር አለመገኘት እና ጥቂት የተገኙ ማህበራት ደግሞ በአንድ ዞን ብቻ 17 ሚሊየን ብር መጠየቃቸው የስርጭት ሂደቱን አስቸጋሪ አድርጎታል ተብሏል፡፡
ችግሩን ለመቅረፍ ከትራንስፖርት ሚኒስቴር ጋር የጋራ ኮሚቴ ተዘጋጅቶ በጨረታ 387 ተሳቢ መኪና ድልድል የተደረገ ቢሆንም በሚፈለገው ልክ አለመሆኑን ቦርዱ አስታውቋል፡፡
የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን የክልል ኮሚሽነሮች በየክልላቸው ያለውን የተፈናቃይ ቁጥር እና የተፈናቃይ ጣቢያዎች እንዲያሳውቁ ጥያቄ መቅረባቸውም ተጠቁሟል፡፡
የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል የተሟላ መረጃ መስጠቱን የገለጸው ቦርዱ፣ ሌሎች 4 ክልሎች በከፊል ምላሽ ሲሰጡ አብዛኞቹ ዘግይተው መስጠታቸው ሂደቱን ከባድ እንዳደረገውም አብራርተዋል፡፡
የፀጥታ ችግር ባለባቸው ክልሎች ማለትም በኦሮሚያ ክልል (በምዕራብ ወለጋ፣ ምስራቅ ወለጋ፣ ሆሮጉድሩ እና ቄለም ወለጋ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል (መተከል እና ካማሼ ዞን)፣ በአማራ ክልል (ኦሮሚያ ልዩ ዞን፣ ሰሜን ሸዋ፣ ሸዋሮቢት፣ ማጀቴ፣ ኤፌሶን ከትግራይ ክልል የሚያዋስኑ 27 ጣቢያዎች) እና በደ/ብ/ብ/ህ ክልል፣ ጉራፈርዳ በ4 ቀበሌዎች) ያለው የፀጥታ ሁኔታ መረጃ ዘግይቶ በመሠጠቱ ሂደቱን አስቸጋሪ አድርጎታል ተብሏል፡፡
የምረጡኝ ቅስቀሳ ከተጀመረ ወዲህ የተለያዩ እጩዎች ለእስር መዳረጋቸውን ቦርዱ አስታውቋል፡፡
በእነዚህ መሰል ችግሮች አጠቃላይ ቦርዱ ባቀደው መሠረት የመራጮች ቁሳቁስ ስርጭት እና ዝግጅት በሚፈለገው ልክ እየሄደ አለመሆኑን የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ አስታውቀዋል፡፡
በመሆኑም ቦርዱ ችግሩን ለማቃለል በአጭር የፅሁፍ መልዕክት ለ35 ሚሊየን ዜጎች መረጃ ማድረስ፣ ለተፈናቀሉ ዜጎች እና ለዝቅተኛ የማህበረሰብ ክፍሎች ግንዛቤ እና ትምህርት ለመስጠት 9 የሲቪክ ማህበራትን ማዘጋጀት እና ከ40 በላይ ቋንቋዎችን በመተርጎም የመራጮች ምዝገባ መረጃ ስርጭት በቀጣይ እንደሚያደርግ የቦርዱ ሰብሳቢዋ ገልፀዋል፡፡
(በሜሮን መስፍን)