መንግስት ድጋፍ እንዲያደርግላቸው ተፈናቃዮች ጠየቁ

ሚያዚያ 19 ቀን 2013 ( ዋልታ) – መንግስት አስቸኳይ ድጋፍ እንዲያደርግላቸው በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከሰዳል ወረዳ ተፈናቅለው ሰሞኑን አሶሳ ከተማ የገቡ ነዋሪዎች ጠየቁ።

ከተፈናቃዮች መካከል ቄስ አዲሱ አባት ለኢዜአ እንዳሉት በሰዳል ወረዳ ለ22 ዓመታት ኖረዋል፡፡

ሚያዚያ 12 / 2013 ዓ.ም በታጠቁ ሽፍቶች በተፈጸመው ጥቃት ያፈሩትን ንብረታቸውን ጥለው ወደ 200 ኪሎ ሜትር በእግራቸው ተጉዘው አሶሳ መግባታቸውን ተናግረዋል፡፡

የጉሙዝ ማህበረሰብ ከለላ በመስጠት ከሽፍታው ታደገውናል፤ የክልሉ ልዩ ሃይል ከጥቃት ሊከላከለን ጥረት አድርጓል ብለዋል፡፡

ህብረተሰቡ ችግሩ ከመፈጠሩ በፊት ለሰዳል ወረዳ አስተዳደር መረጃ እንደሰጠ የተናገሩት ደግሞ ወይዘሮ አየሉሽ አበበ የተባሉ ተፈናቃይ ናቸው፡፡

ወይዘሮ አየሉሽ እንደተናገሩት በጥቃቱ ወቅት እርሳቸውን እና ሌሎች ስምንት ሰዎች ህይወት ያዳኑት በጉሙዝ ማህበረሰብ ድጋፍ ነው፡፡

ወይዘሮ ገነት አታላይ በበኩላቸው፤ ጥቃቱን የፈጸሙት አካላት ላይ እርምጃ በመውሰድ የህግ የበላይነት ሊሰፍን እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡

መንግስት አስፈላጊውን እገዛ እንዲያደርግላቸውም ተፈናቃዮቹ ጠይቀዋል፡፡

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሠላም ግንባታ እና ጸጥታ ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ ሙሳ ሃሚድ እንዳሉት፤ ሽፍታው ተስፋ በመቁረጥ ያለውን ሃይል አሟጦ በመጠቀም ጥቃቱን ማድረሱን አመልክተዋል።

በጥቃቱ የተቃጠሉ መኖሪያ ቤቶች እንዳሉ ያመለከቱት ምክትል ሃላፊው የተጎዱና የተፈናቀሉትን ትክክለኛ ቁጥር የማጣራት ስራ እየተካሄደ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በተፈጠረው ክስተት የክልሉ መንግስት ማዘኑን የገለጹት አቶ ሙሳ ሽፍታው ቡድን በየቦታው በሃገር መከላከያ እና በክልሉ ልዩ ሃይል የሚደርስበትን ጥቃት መቋቋም አቅቶት እየተበታተነ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በወረዳው የተሰማራው የጸጥታ ሃይል በሽፍታው ቡድን ላይ ጠንካራ እርምጃ እየወሰደ መሆኑን ጠቁመው፤ ሽፍታው ከመንግስት አቅም በላይ አይሆንም ብለዋል፡፡

ሽፍታውን የማስወገድ እንቅስቃሴ ከቀናት በኋላ ውጤት እንደሚገኝበት አስታውቀዋል፡፡

ክልሉ የሁሉም ብሄረሰቦች መገኛ መሆኑን ገልጸው በአካባቢው ተጨማሪ ጥቃት እንዳይፈጸም እና ተፈናቃዮች ለመደገፍ የክልሉ መንግስት በትኩረት ይሰራል ብለዋል፡፡

ተፈናቃዮችን ለመደገፍ ከአደጋ ስጋት ስራ አመራር ጋር የተጀመረ ጥረት መኖሩን አቶ ሙሳ አስረድተዋል።