ቦርዱ ከዛሬ ጀምሮ የእጩ መተካት፣ መቀየር፣ መለወጥ እና ማንኛውንም አይነት ማሻሻያ እንደማይቀበል ገለጸ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ

ሚያዝያ 28/2013 (ዋልታ) – የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከዛሬ ጀምሮ የእጩ መተካት፣ መቀየር፣ መለወጥ እና ማንኛውንም አይነት ማሻሻያ እንደማይቀበል ገለጸ፡፡

ቦርዱ ባወጣው መግለጫ በፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና ስነምግባር አዋጅ 1162/2011 አንቀጽ 39 (3) የፖለቲካ ፓርቲ እጩውን መለወጥ ወይም መተካት የሚቻልበት ቀን የእጩ ምዝገባ የጊዜ ሰሌዳ ካለቀ በኋላ ከሆነ ከድምጽ መስጫው ቀን ከአንድ ወር በፊት ባለው ጊዜ ውስጥ ብቻ እንደሆነ ይደነግጋል ብሏል።

በዚህም መሰረት ከዛሬ ከሚያዝያ 28 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ የእጩ መተካት፣ መቀየር፣ መለወጥ እና ማንኛውንም ዓይነት ማሻሻያ የማይቀበል መሆኑን ገልጿል።

እስከአሁን የቀረቡ ከእጩዎች ለውጥ ጋር የተገናኙ ጥያቄዎች የሚስተናገዱ መሆኑን ያሳወቀው ቦርዱ፣ ከዚህ በኋላ የድምጽ መስጫ ወረቀት ህትመት እየተከናወነ በመሆኑ እና በህግ የተቀመጠውም ግዴታ በማብቃቱ ከእጩዎች ምዝገባ ጋር የተገናኘ ማንኛውንም አይነት አቤቱታ መቀበል ማቆሙን አስታውቋል፡፡

ፓርቲዎቹም ይህንን በመረዳት ከዚህ በፊት ያስገቧቸው የለውጥ ጥያቄዎችን ብቻ እንዲከታተሉ አሳስቧል።

ቦርዱ የእጩዎች ምዝገባ ከተጠናቀቀበት ጊዜ ጀምሮ የሚቀርቡ አቤቱታዎችን በመቀበል፣ ችግሮችን በመፍታት እንዲሁም የድምጽ መስጫ ወረቀት ቅደም ተከተል ሎተሪን በማከናወን የእጩዎችን ዝርዝር አጠናቆ ለድምጽ መስጫ ወረቀት ህትመት ሲያዘጋጅ መቆየቱን በመግለጫው አመልክቷል።

(ምንጭ፡-የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ)