ባለስልጣኑ በኮምቦልቻ አየር መንገድ ያስነባውን የአየር ትራፊክ መቆጣጠሪያ ታወር አስመረቀ

በኮምቦልቻ አየር መንገድ ያስነባውን የአየር ትራፊክ መቆጣጠሪያ ታወር

ግንቦት 07/2013 (ዋልታ) – የኢትዮጵያ ሲቪል አቬዬሽን ባለስልጣን በኮምቦልቻ አየር መንገድ ያስነባውን የአየር ትራፊክ መቆጣጠሪያ ታወር አስመረቀ፡፡

በምረቃ ሥነሰርዓት የባለስልጣኑ ዳይሬክተር ጀነራል አቶ ፍቃዱ ውለታው እንደገለጹት፤ መቆጣጠሪያ ታወሩ ከ22 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ ተደርጎበታል፡፡

ግንባታው በሁለት ዓመት እንደተጠናቀቀ ገልጸው፣ የአውሮፕላኖችን እንቅስቃሴ በመቆጣጠር ደህንነታቸውን ለመጠበቅ ያስችላል ብለዋል፡፡

የአቬዬሽን ባለስልጣኑና የአየር መንገዱ  ባለሙያዎች ከዚህ በፊት በሬድዮ መገናኛ ብቻ ግንኙነት ያደርጉ እንደነበር የጠቆሙት አቶ ፍቃዱ፣ ዛሬ የተመረቀው ታወር የግንኙነት መረቡን ዘመናዊ ከማድረጉም ባለፈ የአየር ንብረቱን በቀላሉ ለመረዳትና ፈጣን ምላሽ ለመስጠት እንደሚያስችል ገልጸዋል፡፡

አየር መንገዶች ዘመናዊ መሳሪያ እንዲጠቀሙ በማድረግ ፈጣንና ቀልጣፋ አገልገፍሎት እንዲሰጡ እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

በኢትዮጵያ አየር መንገድ የኮምቦልቻ ቅርንጫፍ ስራ አስኪያጀ አቶ ሰለሞን ቃልአብ በበኩላቸው፣ የአየር መንገዱ ተጠቃሚዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ነው ብለዋል፡፡

በየጊዜው የሚጨምረውን ተገልጋይ ደህንነቱን ጠብቆ ፈጣንና ቀልጣፋ አግልገሎት ለመስጠት ዛሬ የተመረቀው የትራፊክ መቆጣሪያ ታወር ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር ተናግረዋል፡፡

ታወሩ የአካባቢው የአየር ንብረት ሁኔታ ለማወቅ የሚያሳው መሳሪያ ያለው በመሆኑ ባለሙያዎችና ፓይለንቱ በቀላሉ መረጃ ተለዋውጠው ይደረስ የነበረውን መጉላላትም ያስቀራል ብለዋል፡፡

አየር መንገዱ በኮምቦልቻ በቀን ሦስት በረራዎች እንዳሉትና በቀን ከ240 በላይ ሰዎችን እንደሚያጓጉዝ ስራ አስኪያጁ ገልጸዋል፡፡

ኮምቦልቻ ከተማ የኢንዱስትሪና የኢንቨስትመንት ከተማ ከመሆን ጋር ተያይዞ የሚስተዋለውን የደንበኞች ቁጥር መጨመር በሚፈለገው ልክ ለማስተናገድ ከዞኑና ከተማ አስተዳደሩ ጋር እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሰይድ መሃመድ እንዳሉት፤ ለአየር መንገዱ ስራ መቃናት የዞኑ አስተዳደር የሚጠበቅበትን ለማድረግ ዝግጁ ነው፡፡

አቬዬሽን ባለስልጣኑና አየር መንገዱ በዳመና ጊዜ የሚስተዋለውን መጉላላትና ያለውን የተርሚናል እጥረት በማቃለል የኢንዱስትሪ ፓርኩና ፋብሪካዎች ምርት በቀላሉ ወደ ተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎችና ውጭ ለመላክ ምቹ ሁኔታ መፍጠር እንደሚጠበቅባቸው ጠቁመዋል፡፡

ለማንኛውም ግንባታና ማስፋፊያ አየር መንገዱ ለሚጠይቀው መሬት ከከተማ አስተዳደሩ ጋር ተቀናጅተን ፈጣን ምለሽ ለመስጠትም ዝግጁ አድርገናል ብለዋል፡፡

በምርቃት ሥነ ስርዓቱ የፌደራል፣ ክልል፣ ዞንና ከተማ አስተዳደሩ አመራሮች፣ የሐይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና ባለድርሻ አካላት መገኘታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡