በአንድ ግለሰብ ቤት በተደረገ ፍተሻ 112 ሺህ ሃሰተኛ የብር ኖት ተገኘ

ሃሰተኛ የብር ኖት

ግንቦት 09/2013 (ዋልታ) – በዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር በፃግብጂ ወረዳ በአንድ ግለሰብ ቤት በተካሄደ ፍተሻ 110 ሺህ ባለ ሁለት መቶ ብር እና 2 ሺህ ባለ መቶ ብር በድምሩ 112 ሺህ ሃሰተኛ የብር ኖት መገኘቱን ፖሊስ አስታወቀ።

የወረዳው ፓሊስ ፅህፈት ቤት ሃላፊ ዋና ኢንስፔክተር ደሳለኝ አለሙ እንደገለፁት፣ ሃሰተኛ የብር ኖቱ የተገኘው በወረዳው 02 ቀበሌ በለቃ ተብሎ በሚጠራ አካባቢ ነዋሪ ከሆነ አንድ ግለሰብ ቤት ነው።

በቀበሌው ህገ ወጥ ድርጊት ለመፈፀም የተዘጋጀ ግለሰብ እንዳለ ከህብረተሰቡ በደረሰ ጥቆማ መሰረት የፀጥታ አካል ባደረገው ፍተሻ የሃሰተኛ የብር ኖቱ መገኘቱን ተናግረዋል።

ከሃሰተኛ የብር ኖቱ በተጨማሪ አንድ ሽጉጥ መገኘቱንም ገልጸዋል።

ተጠርጣሪው ለጊዜው በመሰወሩ ፖሊስ ክትትል እያደረገበት መሆኑን ዋና ኢንስፔክተር ደሳለኝ መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።