ዶ/ር አብርሃም በላይ የመሰቦ ሲሚንቶ ፋብሪካ የስራ እንቅስቃሴ ጎበኙ

ዶ/ር አብርሃም በላይ

ግንቦት 12/2013 (ዋልታ) – የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ዋና ስራ አስፈፃሚ ዶ/ር አብርሃም በላይ የየመሰቦ ሲሚንቶ ፋብሪካ አጠቃላይ ነባራዊ ሁኔታና ቀጣይ የስራ አቅጣጫ ለመስጠት በስፍራው ተገኝተው ጉብኝት አድርገዋል።

ዶ/ር አብርሃም በላይ በጉብኝታቸው ወቅት ከፋብሪካው የስራ ሃላፊዎችም ጋር የተወያዩ ሲሆን፣ የመሰቦ ሲሚንቶ ፋብሪካ ከመስፍን ኢንዱስትሪያል ኢንጅነሪንግ ጋር በመተባበር እየሰራ ያለውን የጥገና ስራዎችና የምርት ሁኔታ በተሻለ ፍጥነት የሚፈፀምበት ሁኔታ በተመለከተ አቅጣጫ ተቀምጧል::

ከዚህ በተጨማሪም የሲሚንቶ ተደራሽነት በትግራይ ህዝብ ፍላጎትና ልማት ቅድሚያ ሰጥቶ እንዲሰራ፣ ፍትሃዊ የሆነ ተደራሽነት እንዲኖርና አዳዲስ የስራ ዕድል መፍጠር ላይ ትኩረት ሰጥቶ እንዲሰራ የሚያስችል ማስተካከያ እንደሚደረግ ተገልጿል::

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ዋና ስራ አስፈፃሚ ዶ/ር አብርሃም በላይ በመቐለና አካባቢው ከተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው በግዜያዊ መጠለያ የሚገኙ ዜጎች ያሉበትን ሁኔታም ተመልክተዋል።

እንዲሁም እስካሁን የተደረጉ ሰብአዊ ድጋፎች በተግባር የተመለከቱ ሲሆን፣ በመሰቦ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እና በኤልሻዳይ ጊዜያዊ መጠለያዎችም ጉብኝት ተደርጓል።

ከመጠለያዎቹ ተወካዮችና አስተባባሪዎች ጋር በተደረገ ምክክርም በሰብአዊ ድጋፎች ረገድ ያጋጠሙ ችግሮች ታርመው ፍትሓዊ ተደራሽነትን አስተማማኝ በማድረግ ድጋፉን ለማስቀጠል የሚያስችል አቅጣጫ መቀመጡን ኢዜአ ዘግቧል።