የ”ብሔራዊ ክብር በሕብር” አስተባባሪ ግብርኃይል በእንግሊዝ ኤምባሲ ተገኝቶ መልዕክቱን ለእንግሊዝ መንግሥት አደረሰ

                                                   የ”ብሔራዊ ክብር በሕብር” አስተባባሪ ግብርኃይል

ግንቦት 18/2013 (ዋልታ) – በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ የሚደረገውን ጣልቃ ገብነት በመቃወም የ”ብሔራዊ ክብር በሕብር” አስተባባሪ ግብርኃይል በዛሬው ዕለት በእንግሊዝ ኤምባሲ ተገኝቶ መልዕክቱን ለእንግሊዝ መንግሥት አደረሰ፡፡

የብሔራዊ ክብር በኅብር ግብርኃይል ለእንግሊዝ ኤምባሲ ባደረሰው መልእክት ኢትዮጵያ እየገነባች ያለችውን ታላቁ የህዳሴ ግድብ አስፈላጊነት በመግለጽ፣ የሀገሪቱን የምርጫ ፍላጎት እና ሉዓላዊነት እንዲያከብሩ፣ በውስጥ ጉዳይ ጣልቃ እንዳይገቡም ጠይቋል፡፡

ግብርኃይሉ ሽብርተኝነትን ለመዋጋት ኢትዮጵያ የምታደርገውን ጥረት መደገፍ እንደሚገባ በመልዕክቱ አስተላልፏል፡፡

የግብርኃይሉ የተቃውሞ እንቅስቃሴ “ከሀገራችን ላይ እጃችሁን አንሱ” የሚል መሪ ሃሳብ ያነገበ ሲሆን፣ ለአሜሪካ ኢምባሲ እና ለአውሮፓ ኅብረት በተለያዩ የመረጃ ማስተላለፊያ መንገዶች መልእክቱ እንዲደርስ ማድረጉ ተገልጿል፡፡

በኢምባሲው ከእንግሊዝ የፖለቲካ ቃል አቀባይ እና ካውንስል ጋር የአንድ ሰዓት ውይይት ተደርጓል ተብሏል፡፡ በዚህም ግብርኃይሉ በተለያዩ ጉዳዮች ትክክለኛ መረጃ ለመስጠት ጥረት ማድረጉ ተጠቅሷል፡፡

እንደ አሚኮ ዘገባ መልእክቱ ለእንግሊዝ መንግሥት እንደሚደርስም ቃል ተገብቷል ነው የተባለው።