ህዝበ ሙስሊሙ በቅዱሱ የረመዳን ወር ያሳየውን የመረዳዳት እሴት አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባዋል – አቶ እርስቱ ይርዳው

አቶ እርስቱ ይርዳው

ግንቦት 04/2013 (ዋልታ) – የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር እርስቱ ይርዳው ህዝበ ሙስሊሙ በቅዱሱ የረመዳን ጾም ወር ያሳየውን የመረዳዳት እና የመደጋገፍ እሴት አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ ገለጹ፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ የኢድ አል ፈጥር በዓልን በማስመልከት ለመላው የእስልምና እምነት ተከታዮች የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

የኢትዮጵያ ህዝቦች አብሮነት፣ ወንድማማችነት እና እህታማማችነት ባህል እንዲጎለብት ሁሉም ቤተ እምነቶች የሚጠበቅባቸውን ሁሉ እየተወጡ መሆኑን የጠቆሙት አቶ እርስቱ፣ ይህ መልካም ምግባር ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ሀገሪቱ በልዩ ልዩ ፈተናዎች ውስጥ እንደምትገኝ ገልጸው መላው የክልላችን እና የሀገራችን ህዝቦች ሀገራችን ወደ ከፍታ ማማ እንድትወጣ ሚናውን ሊወጣ ይገባልም ብለዋል፡፡

በየአካባቢው የተፈናቀሉ ዜጎችን በመርዳት እና በመደገፍ የተቸገሩ ወገኖች ማገዝ ከምንጊዜውም በላይ ከህዝበ ሙስሊሙ ይጠበቃል ነው ያሉት፡፡

በጤና ችግር ውስጥ የሚገኙና ድጋፍ የሚሹ ዜጎችን በመርዳት የሀገሪቱ አንድነት ተጠብቆ የበለጸገች ሀገር ለመፍጠር የሁሉንም አካላት ጥረት እንደሚጠይቅ ጠቁመዋል፡፡

ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ በመልዕክታቸው መጪው ሀገራዊ ምርጫ ፍጹም ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ሰላም ወዳዱ ህዝበ ሙስሊም እና መላው የሀገሪቱ ህዝቦች የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በአሁኑ ሰዓት መላው የአለምን ህዝብ እያስጫነቀ ያለው የኮሮና ቫይረስ የምንወዳቸውን ዜጎች ህይወት እየቀጠፈ መሆኑን ገልጸው ህብረተሰቡ ለቫይረሱ አጋላጭ ከሆኑ ድርጊቶች ሊርቅ ይገባልም ብለዋል፡፡