የአማራ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር አገኘሁ ተሻገር ለኢድ አልፈጥር በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ

ግንቦት 04/2013 (ዋልታ) – የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አገኘሁ ተሻገር ለእስልምና እምነት ተከታዮች የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ርእሰ መሥተዳድሩ በመልዕክታቸው እንደገለፁት የረመዳን ፆም በሕዝበ ሙስሊሙ በከፍተኛ ትኩረትና ሀይማኖታዊ ሥነምግባር የሚፆም ታላቅ የፆም ወቅት ነው።
“የኢድ አልፈጥር በዓል ስናከብር ሃይማኖታዊ አስተምህሮቱ በሚያዘውና በሚፈቅደው መሠረት ስለሀገራችን ሰላምና አንድነት እየተጋን የራሳችንንም አስተዋፅኦ እያበረከትን ሊሆን ይገባል” ርእሰ መሥተዳድር አገኘሁ ተሻገር “በዘንድሮው የረመዳን ፆም ሕዝበ ሙስሊሙ ስለ ሀገራችን ሰላምና አንድነት አብዝተው ፈጣሪያቸውን የተማፀኑበት በተለይም በክልላችን በ ባቲ ከተማ ተጀምሮ ከዚያም ከሚሴ፣ ሐርቡ፣ ገርባ፣ ኮምቦልቻ፣ ደሴ፣ መርሳ፣ ወልዲያ፣ ባሕር ዳር በአንድነት አንዱ ከሌላው ጋር በመረዳዳት፣ በፍቅር የጎዳና ላይ አፍጥር ፕሮግራም የተካሄደበት ዓመት ነው” ብለዋል።
“የኢድ አልፈጥር በዓል ስናከብር ሃይማኖታዊ አስተምህሮቱ በሚያዘውና በሚፈቅደው መሠረት ስለሀገራችን ሰላምና አንድነት እየተጋን የራሳችንንም አስተዋፅኦ እያበረከትን ሊሆን ይገባል” ነው ያሉት።
በዓሉ ሲከበርም የሕዝቡን የመቻቻልና የመተሳሰብ እንዲሁም በአንድነት የመኖር እሴቱን በመሸርሸር ማንነትን መሰረት ያደረገ ጥቃት የሚፈፅሙ ኃይሎችን ለመታገል የሚደረገውን ጥረት በመደገፍና በዚሁ ጥቃት የተፈናቀሉትን ወገኖቻችንን ደግሞ ለመደገፍና ለማቋቋም የሚደረገውን ጥረት በማገዝ ሊሆን እንደሚገባ ገልጸዋል።
“ከምስኪኖች ጋር ተካፍሎ በመዋል ከክርስቲያን ወንድሞቻችሁ እና ወዳጅ ዘመዶች ጋር ደግሞ በዓሉን በዝያራ በማክበር ሊሆን ይገባል” ብለዋል።
የተለያዩ ኃይሎች በየትኛውም አጋጣሚ የሃይማኖትን አጀንዳ እየመዘዙ ሊያጋጩን ይሞክራሉ ፤ ይህንን ሕዝበ ሙስሊሙም መላው ሕዝብ ጠንቅቆ ማወቅ እንደሚገባም ነው ያስገነዘቡት።
“የብሔር እና መሠል ግጭቶች መነሻ ምክንያቶች በመንግሥት ጥረት እየተቀረፉና መፍትሔ እየተሰጣቸው ሲሄድ ጠላቶቻችን ደግሞ የሃይማኖት አጀንዳን እያነሱ ሊያጋጩን ይሞክራሉ። በመሆኑም እምነቶችን መሰረት አድርገው ሊከፋፍሉን የሚፈልጉ ሀይሎችን በመታገል ሰላምና ወንድማማችነትን እንዲሁም መቻቻልን የበለጠ ለማጠናከር ተጋግዘን መስራት ይኖርብናል” ብለዋል በመልዕክታቸው።
(ምንጭ፡- አሚኮ)