ለብሪክስ አባል ሀገራት መጭው ጊዜ ብሩህ ነው

ነሐሴ 28/2015 (አዲስ ዋልታ) በዚህ በያዝነው 2023 ዓ.ም የሳኡዲ አረቢያ ኢኮኖሚ፣ ከየትኛውም አገር በበለጠ ፍጥነት፣ ሲያድግ የነበረ ኢኮኖሚ ነው ተብሎለታል፡፡ የGeneral Authority for Statistics (GASTAT) ሪፖርት እንደሚጠቁመው በ2022 አምናም፣ በ3ኛው ሩብ አመት፣ ከቀደመው አመት ጋር ሲነጻጸር የሳኡዲ አጠቃላይ አመታዊ ምርት በ8.8 ከመቶ ሲያድግ ነበር፡፡

ለ2023 ዓ.ም መንግስት የመደበው አመታዊ በጀት 1 ነጥብ 114 ትሪሊየን የሳኡዲ ሪያል (297 ቢሊየን ዶላር) ሲሆን ታገኛለች ተብሎ የተገመተው አመታዊ ገቢዋ ደግሞ 1 ነጥብ 130 የሳኡዲ ሪያል ወይም 4 ነጥብ 2 ቢሊየን ዶላር ነበር፡፡

የነዳጅ ዋጋ በመጨመሩ ምክንያት እና አገሪቱ ለቢዝነስ የተመቹ አዳዲስ ፖሊሲዎችን በመዘርጋቷ ሳኡዲ አረቢያ ከሁሉም ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት የምታስመዘግብ አገር ሆና እንደምትቀጥል የኢኮኖሚ ሊቆች እየተነበዩ ነው፡፡

Article IV consultation report እንደሚጠቁመው የአገር ውስጥ አጠቃላይ ምርት በ7 ነጥብ 6 ከመቶ ማደጉን የሚቀጥል ሲሆን ይህም ባለፉት 10 አመታት በሳዑዲ ታይቶ የማያውቅ የእድገት መጠን ነው ተብሏል፡፡

ባለፈው አመት በሳኡዲ የዋጋ ግሽበት ከ3ከመቶ በታች ነበር፡፡ አገሪቱ ይህን የኢኮኖሚ ግስጋሴዋን ወደፊትም ለማስቀጠል ቪዥን 2030 የሚል ዘመቻ ከጀመረች ሰነባብታለች፡፡ የቪዥን 2030 ዋነኛ አላማዎች የአገሪቱን ኢኮኖሚ፣ ከነዳጅ ጥገኛነት አላቆ፣ በርካታ ዘርፎችን ያካተተ ጠንካራ ኢኮኖሚ መገንባት፣ የ40 ሚሊየን የሳዑዲ ዜጎችን ህይወት የበለጠ ማሻሻል እና ሳኡዲ አረቢያ በአለም ላይ ያላትን ቦታ አጠናክሮ ማስቀጠል ናቸው፡፡

ከቪዥን 2030 ውጥኖች ግንባር ቀደሙ በሀገሪቱ ሰሜን ምእራብ በ500 ቢሊየን ዶላር ሊገነባ የታቀደው እና ኒኦም (NEOM) የተሰኘው እጅግ ዘመናዊ ከተማ ነው፡፡ ይህ 9 ሚሊየን ሰዎች ይኖሩበታል የተባለው እና በቀይ ባህር ዳርቻ የሚገነባው እጅግ ዘመናዊ ከተማ 26.5 ካሬ ሜትር ስፋት ይኖረዋል፡፡ የአካባቢውን ንጽህና ለመጠበቅ፣ መኪና የማይገባበት እና መቶ በመቶ በታዳሽ ሀይል የሚንቀሳቀስ ከተማ ይሆናል ነው የተባለው ኒኦም፡፡

እንግዲህ ይህች በፈጣን የኢኮኖሚ እድገት፣ ከአለም አንደኛዋ፣ እጅግ ሀብታሟ ሳኡዲ አረቢያ ነች፡፡ ኢትዮጵያን ጨምሮ የብሪክስ አባል እንደትሆን ከሌሎች 5 አገራት ጋር የተጋበዘችው፡፡

ስድስቱ አገራት ትክክለኛ የብሪክስ አባሎች የሚሆኑት ከመጭው ጥር ጀምሮ ነው፡፡ ሳኡዲ ግን ገና እውነተኛዋ አባል ሳትሆንም በፊት ጥር ከመድረሱም በፊት አዲሱ ብሪክስ ውስጥ 16 ቢሊየን ዶላር ኢንቨስት ለማድረግ ወስናለች፡፡

ከአዳዲሶቹ 6 የብሪክስ አባላት አንዷ የሆነችው የተባበሩት አረብ ኤሚሬትስም፣ ልክ እንደ ሳኡዲ በፍጥነት እያደገ ያለ ኢኮኖሚ የገነባች፣ የዋጋ ግሽበት ከ3 ፐርሰንት በታች የሆነባት፣ የስራ አጥ ቁጥርም ከ3 ፐርሰንት በታች የሆነባት፣ ዜጎች በአመት በነፍስ ወከፍ ከ40 ሺሕ ዶላር በላይ የሚያገኙባት፣ ዱባይን የመሰለ የመካከለኛው ምስራቅ ብቻ ሳይሆን የአለም ኢኮኖሚም የሚዘወርባትን ከተማ የሰራች ትልቅ ጠንካራ አገር ነች፡፡

ሌላዋ አዲስ አባል አርጀንቲናም ከብራዚል ቀጥሎ በደቡብ አሜሪካ ሁለተኛው ጠንካራ ኢኮኖሚ ያላት አገር ነች፡፡ እነ ሜሲን፣ እነ ማራዶናን ለአለም ያበረከተች አገር ነች፡፡ ያለፈውን አመት የአለም የእግር ኳስ ዋንጫ የወሰደች ዝነኛ አገር ነች፡፡

ሌላይቷ አዲስ አባል ግብጽም ከናይጄሪያ ቀጥሎ በአፍሪካ 2ኛውን ትልቁን ኢኮኖሚ የገነባች አገር ነች፡፡ የጥንታዊ ስልጣኔ ባለቤት ነች፡፡ የአስደናቂ ፒራሚዶች እና የፈርኦኖች አገር ነች፡፡ ኢራንም የፐርሽያን ስልጣኔ ለአለም ያስተዋወቀች፣ ፐርሺያን ኤምፓየር የሚባል ገናና ግዛተ መንግስት የነበራት፣ የሺአውን አለም የምትመራ፣ በመካከለኛው ምስራቅ ጎረቤቶቿ ብቻ ሳይሆን በምእራቡም አለም የምትፈራ ለክብሯ ከማንም ጋር ለመፋለም ወደ ኋላ የማትል፣ የመካከለኛው ምስራቅ ሀያል አገር ነች፡፡

የቀደሙት መስራቾቹ የብሪክስ አባላት (ብራዚል፣ ሩሲያ፣ ህንድ፣ ቻይና፣ እና ደቡብ አፍሪካ) ማስታወቂያ አያስፈልጋቸውም፡፡ በአጠቃላይ የአገር ውስጥ ምርት (2023)፣ ቻይና የአለም 2ኛዋ ጠንካራ ኢኮኖሚ (17.7 ትሪሊየን ዶላር) ነች፣ በጥቂት አመታት እድሜ የአሜሪካን አመታዊ ምርት ( 23.3 ትሪሊየን ዶላር) በልጣ፣ ጠንካራዋ የአለም ኢኮኖሚ እንደምትሆን ይጠበቃል፡፡ ህንድ፣ በአለም 5ኛዋ ጠንካራ ኢኮኖሚ (3.1 ትሪሊየን ዶላር) ነች፡፡ አዲሷ የብሪክስ አባል ግብጽ፣ ከናይጄሪያ (514.05 ቢሊየን ዶላር) ቀጥሎ፣ በአፍሪካ 2ኛዋ ትልቋ ኢኮኖሚ ነች፡፡ ደቡብ አፍሪካ፣ በ394.28 ቢሊየን ዶላር፣ 3ኛዋ የአፍሪካ ግዙፉ ኢኮኖሚ ነች፡፡

ኢትዮጵያ እንግዲህ ከእነዚህ ግዙፎች ጋር ታላላቅ ህዝቦች እና አገሮች ተርታ የተሰለፈችበት መድረክ ነው ብሪክስ! ኢትዮጵያም፣ እንደ ብዙዎቹ የስብስቡ አባላት፣ በፍጥነት እያደገ ያለ፣ በከፊል ሰሀራ አፍሪካ 4ኛው ጠንካራ ኢኮኖሚ (126.2 ቢሊየን ዶላር) የገነባች፣ የሺሕ ዘመናት የስልጣኔ እና የነጻነት ታሪክ ያላት፣ የአፍሪካውያን የነጻነት ምልክት፣ የሆነች አገር ነች፡፡

እነዚህ ሁሉ፣ ሀብታቸውን፣ ታሪካቸውን፣ የመበልጸግ ጉጉታቸውን ይዘው፣ ብሪክስ በተሰኘ ማህበር ወይም እድር ውስጥ ተሰባስበዋል፡፡ ከአለም ህዝብ ወደ 50 ከመቶ የሚጠጋው፣ የእነዚህ አገሮች ዜጋ ነው፡፡ እነዚህ 11 የማህበሩ አባላት፣ ለአለም ኢኮኖሚ የሚያበረክቱት ድርሻም፣ ከ30 ፐርሰንት በላይ ነው፡፡ ግማሹን የአለም ህዝብ ይዘህ፣ ሲሶውን የአለም ኢኮኖሚ አዋጥተህ፣ በአለም መሪ እንጂ፣ ተመሪ አትሆንም፡፡ የአንድ አገር ወይም የአንድ ሀብታም መጫወቻ አትሆንም፡፡  የዚህ ብሪክስ የተሰኘ የአገሮች እድር አባል ለመሆን፣ ከ40 በላይ አገራት አመልክተው ነበር፡፡ ታሪካቸውን፣ የአህጉር ውክልናቸውን፣ በአለም ተሰሚነታቸውን፣ ተመልክተው፣ 6ቱን ብቻ ተቀበሉ፡፡ ከ6ቱ አንዷ፣ ኢትዮጵያ ሆነች፡፡ የዚህ መልካም እድር አባል በመሆኗ፣ ኢትዮጵያ፣ ብድር የማግኘት፣ ቴክኖሎጂ የማግኘት፣ ሰፊ ገበያ የማግኘት፣ ተጽእኖን የመቋቋም፣ ለአንድ አላማ በጋራ የመቆም እድሏ ይጨምራል፣ አቅሟ የጨምራል፣ እድገቷ ይጨምራል፡፡

6ቱ አባላት ከተመረጡ በኋላ፣ የመስራቾቹ 5ቱ አገራት መሪዎች፣ አዲሶቹን የእድሩ አባላት፣ ሞቅ ባለ ስሜት፣ እንኳን ደስ ያላችሁ ብለዋቸዋል፡፡ የቻይናው መሪ የተናገሩት ግን፣ የሁሉንም ልብ የሚያሞቅ ነበር፡፡

ለብሪክስ እና ለአባሎቹ፣ መጭው ጊዜ፣ ብሩህ ነው!!!

መልካም ጊዜ፣ ለብሪክስ አባላት!

መልካም ጊዜ ለአፍሪካ!

መልካም አዲስ አመት ለኢትዮጵያ!!