አትሌቶች በቡዳፔስት ቆይታቸው የኢትዮጵያዊነት የመንፈስ ከፍታን በሚገባ ያሳዩበት ነው – ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ

ነሐሴ 29/2015 (አዲስ ዋልታ) የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ አትሌቶች በቡዳፔስት ቆይታቸው በዓለም አደባባይ ፍቅርን፣ መከባበርንና የኢትዮጵያዊነት የመንፈስ ከፍታን በሚገባ ያሳዩበት እንደነበር ገለጹ።

በ19ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ለተሳተፈው የአትሌቲክስ ልዑክ ቡድን የእውቅናና የሽልማት ሥነ ሥርዓርት በብሔራዊ ቤተ-መንግስት ተካሂዷል።

በመርኃ ግብሩ የኢፌዲሪ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ እንዲሁም ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎችና የስፖርት ቤተሰቦች ተገኝተዋል።

የእለቱ የክብር እንግዳ የሆኑት ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ አትሌቶች በቡዳፔስት ቆይታቸው በዓለም አደባባይ ፍቅርን፣ መከባበርንና የኢትዮጵያዊነት የመንፈስ ከፍታን በሚገባ ያሳዩበት እንደነበር አንስተው ለተገኘው ድል ሁሉንም የልዑካን ቡድን አመስግነዋል።

በቀጣይ ከአትሌቲክስ ስፖርት በዘለለ በሌሎችም መስራት እንደሚገባ ገልጸው ለፓርሱ ኦሎምፒክ ከወዲሁ ዝግጀት እንዲከናወን ጥሪ አቅርበዋል።

የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ቀጀላ መርዳሳ በበኩላቸው አትሌቶች በከባድ የአየር ንብረት ወበቅ ተቋቁመው የላቀ ውጤት በማምጣታቸው ምስጋና ይገባቸዋል ብለዋል።

በተከናወነው የሽልማት መርኃ ግብር ወርቅ ላስገኙት አትሌት ጉዳፍ ፀጋዬ እና አማኔ በሪሶ በየግል 1 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

የብር ሜዳሊያ ላስገኙ አራት ተወዳዳሪዎች በየግል አንድ ሚሊዮን ብር የተበረከተላቸው ሲሆን ለነሐስ ሜዳሊያ ባለቤቶች 700 መቶ ሺሕ ብር ተበርክቷል።

ለተሳታፊ አትሌቶችና ዲፕሎማ ደረጃን ይዘው ላጠናቀቁ እንደየደረጃቸው ከ50 ሺሕ እስከ 320 ሺሕ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

ለአሰልጣኞች እና ልዑካን ቡድኑ ጨምሮ እስከ 14 ሚሊዮን ብር ሽልማት በመርኃግብሩ ተበርክቷልም የተባለው።

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ረ/ኮ ደራርቱ ቱሉ ከዓለም አትሌቲክስ ለስፖርቱ ባበረከተችው አስተዋፅኦ የተበረከተላትን ሽልማት ለፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ማስረከቧም ተመላክቷል፡፡

በሐብታሙ ገደቤ