መንግሥት በትግራይ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች ሰብአዊ ድጋፍ ለማድረግ እየሠራ ነው

የፌዴራል መንግሥት በትግራይ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች ሰብአዊ ድጋፍ ለማድረግ እየሠራ መሆኑን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ገልጿል፡፡

የኢፌዴሪ መንግሥት ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጋር በመተባበር በትግራይ ክልል ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች ድጋፍ እንዲደርስ ለማድረግ እየሠራ ነው ተብሏል፡፡

ወደ ክልሉ የሚላከው የሰብአዊ ድጋፍ በአንዳንድ ከተሞች ባለው ጦርነት እንቅፋት ገጥሞታል ተብሎ የሚወራው እውነት እንዳልሆነ እና የመከላከያ ሠራዊት አካባቢውን ለማረጋጋት እየሠራ ላለው ሥራ እውቅና ካለ መስጠት የሚመነጭ መሆኑ ተገልጿል፡፡

የሕወሓት ቡድን በመከላከያ ሠራዊት ላይ እርምጃ እንደተወሰደ በሰላም ሚኒስቴር የሚመራው እና የሚደረገው ሰብአዊ ድጋፍን የሚቆጣጠር ከፍተኛ ኮሚቴ መቋቋሙ ይታወሳል፡፡

ኮሚቴው ባደረገው ቴክኒካዊ የዳሰሳ ጥናት መሠረት የሰብአዊ ድጋፉ እየተደረገ መሆኑ ተገልጿል፡፡

ባለፈው ወር ውስጥ የመጀመሪያ ዙር ሰብአዊ ድጋፍ እና የሕክምና ቁሳቁሶች ወደ ዳንሻ፣ ወልቃይት፣ ቃፍታ/ሁመራ እና ደባርቅ አካባቢዎች እንደተላከ ተገልጿል፡፡

ባለፈው ማክሰኞ ዕለት በ44 የጭነት መኪኖች የተጫኑ 18 ሺህ 200 ኩንታል ለምግብ ፍጆታ የሚውሉ እህሎች ወደ ተለያዩ የትግራይ ከተሞች መላካቸውንም ጽ/ቤቱን ዋቢ አድርጎ ኢዜአ ዘገቧል፡፡