ጃፓን ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የንግድ እና ኢንቨስትመንት ትብብር ማጠናከር እንደምትፈልግ አስታወቀች

ጃፓን ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የንግድና ኢንቨስትመንት ትብብር ማጠናከር እንደምትሻ በኢትዮጵያ የአገሪቷ አምባሳደር ኢቶ ታካኮ ገለጹ።

አምባሳደሯ አገራቸው የኮቪድ-19 ወረርሽኝና የአንበጣ መንጋን ለመከላከል ድጋፍ እንደምታደርግም አስታውቀዋል።

ኢትዮጵያና ጃፓን 90 ዓመታትን ያስቆጠረ የዲፕሎማሲ ግንኙነት ያላቸው ሲሆን፤  በትምህርት፣ በሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ በግብርናና በማህበራዊ መስኮችም ትብብር ያደርጋሉ።

ጃፓን በዓለም አቀፍ የልማት ትብብር ኤጀንሲዋ /ጃይካ/ አማካኝነት ለልማት ፕሮጀክቶች የገንዘብና የቴክኒክ ድጋፍ እንደምታደርግ መረጃዎች ያመለክታሉ።

አምባሳደር ታካኮ እንደተናገሩት ጃፓን ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የንግድና ኢንቨስትመንት መስኮች ግንኙነት ማጠናከር ትፈልጋለች።

የጃፓን ባለሀብቶች በኢትዮጵያ መዋዕለ ነዋያቸውን እንዲያወጡ ድጋፍ እንደሚደረግም ገልጸዋል።

ጃፓን በፖለቲካ፣ በደህንነትና በባህል ስፖርት ያላትን ትብብር ማጎልበት ትፈልጋለችም ብለዋል።

አገራቸው ለኢትዮጵያዊያን በተለያዩ የትምህርት ዘርፎች በተለይም በቢዝነስ መስክ የምትሰጠውን ነጻ የትምህርት ዕድል እንደምታሳድግም ገልጸዋል።

ጃፓን በኢትዮጵያ የኮቪድ-19 ወረርሸኝና የአንበጣ ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ ሰብዓዊ ድጋፍ እንደምታደርግም አምባሳደሯ ተናግረዋል።

በጃፓን ዓለም አቀፍ የልማት ትብብር ኤጀንሲ /ጃይካ/ በቀጣዩ የአውሮፓዊያን ዓመት ድጋፍ የሚያደርግባቸው የትብብር መስኮች ተለይተው በቅርቡ ይፋ እንድሚደረግ ለኢዜአ ገለጸዋል፡፡