መንግስት ለሰብዓዊ መብቶች መከበር በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑን አስታወቀ


መስከረም 25/2016 (አዲስ ዋልታ) የኢትዮጵያ መንግስት ለሰብዓዊ መብቶች መከበር በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑን አስታወቀ፡፡

የኢፌዴሪ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በዛሬው ዕለት ባወጣው መግለጫ ተዓማኒነት ባለው አገር በቀል እና ዓለም አቀፍ ደረጃውን በጠበቀ የሽግግር ፍትህ አሰራር ፍትህን፣ ይቅርታን እና እውነትን ለማፈላለግና ለማረጋገጥ መንግስት እየሰራ መሆኑን ገልጿል፡፡

ለዚህም በቅርቡ የሽግግር ፍትህ ፖሊሲ ዶክመንት በሚኒስትሮች ምክር ቤት እንደሚጸድቅ አስታውቋል፡፡

“ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን የሽግግር ፍትህን በተሟላ መልኩ ተግባራዊ ለማድረግ መንግስት የጀመረውን ቀጣይነት ያለው ጥረት አጠናክሮ ለማስቀጠል ቁርጠኛ ነው” ብሏል በመግለጫው።

ከዚህ በተጨማሪም ተጠያቂነትን ለማረጋገጥና ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን፣ መንግስት በከፍተኛ ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት ትግበራን፣ የሀገራዊ ምክክር ሂደቱን፣ የመልሶ ግንባታ እና ተሓድሶ እንዲሁም ሰላምን ለማጠናከር በፍጥነት ተግባራዊ የማድረግ ስራን እንደሚሰራ መጥቀሱን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል፡፡