ምርጫ ቦርድ የምርጫ ሰላምን ከማስከበር አንፃር ያለበትን ኃላፊነት እንደሚወጣ አስታወቀ

መጋቢት 17/2013 (ዋልታ) – የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የምርጫ ሰላምን ከማስከበር አንፃር ያለበትን ኃላፊነት እንደሚወጣ አስታውቋል።

ምርጫ ቦርዱ በየወቅቱ ለሚያገረሽ ግጭት መነሻ በሆኑ ቀበሌዎች ስር የታቀፉ ጣቢያዎች ተከፍተው የምርጫ ሂደት እንዳይደረግባቸው የወሰነውን ውሳኔ እንደማይቀበለው በሶማሌ ክልላዊ መንግስት ርእሰ መስተዳድር ጽህፈት ቤት በላከው ደብዳቤ እንዳስታወቀ ገልጿል።

ይህንን ጉዳይ አስመልክቶም ምርጫ ቦርዱ ለክልሉ መንግስት ምላሽ መስጠቱን አስታውቋል።

በዚህም ቦርዱ በአፋር እና በሶማሌ ክልላዊ መንግስታት በኩል አከራካሪ የሆኑ ቦታዎች ላይ ምርጫ ጣቢያ ላለመክፈት የወሰነው የምርጫ ሰላምን ከማስከበር አንፃር ያለበትን ኃላፊነት ለመወጣት መሆኑን አስታውቋል።

በተጠቀሱት ስፍራዎች የሚኖሩ ዜጎች ያላቸው መሰረታዊ የመምረጥ መብታቸውን በሰላማዊ ድባብ ውስጥ ተግባራዊ ማድረግ እንዲችሉ ከምርጫ ክልላቸው ሳይወጡ በአቅራቢያቸው ባሉ ጣቢያዎች መመዝገብ እንዲችሉም መሆኑም ምርጫ ቦርዱ በደብዳቤው አስታውቋል።

ቦርዱ ውሳኔውን ከመስጠቱ በፊትም ከሚመለከታቸው አካላት ምክረ ሀሳብ መጠየቁም ተገልጿል።

በመሆኑም በሶማሌ ክልል መንግስት ተቃውሞ ያቀረበበት የቦርዱ ውሳኔ የመራጮች እና የምርጫ ሂደትን በተለይም የምርጫ ሰላምን ብቻ የሚመለከት መሆኑን በመረዳት የመተባበር ግዴታውን እንዲወጣ ምርጫ ቦርዱ አሳስቧል።