ምርጫ 2013 ፍትሓዊና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን የሲቪክ ማኅበራትና የዜጎች ነፃ ተሳትፎ ተጠየቀ

ግንቦት 25/2013 (ዋልታ) – ምርጫ 2013 ፍትሓዊና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን የሲቪክ ማኅበራትና የዜጎች ነፃ ተሳትፎ ተጠየቀ።

“የዜጎች፣ የሲቪክ ማኅበራትና የፖለቲካ ፓርቲዎች ሚና ለሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ” በሚል መሪ ሀሳብ በደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ ምክክር እየተደረገ ነው።

በመድረኩ ላይ የተገኙት የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ሙሉ ነጋ (ዶ/ር) በምርጫ 2013 እንደሀገር የሁሉም አሸናፊነት እንዲረጋገጥ መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።

ሚኒስትር ዴኤታው በምርጫ 2013 ዙሪያ የሚደረጉ የውይይት መድረኮች በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ለቀጣዮቹ ሦስት ሳምንታት እንደሚቀጥል ጠቁመው፣ ከየመድረኮቹ የሚገኙ ሀሳቦች ለዩኒቨርሲቲዎች ቀጣይ የምርምር ሥራ መነሻ ይሆናሉ ብለዋል።

መድረኩ ምርጫ 2013ን ሰላማዊ ማድረግ የሚቻልበት ስልት ላይ መመካከርን ዋነኛ አጀንዳው ማድረጉም ተገልጿል።

በመድረኩ ንግግር ያደረጉት የደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ንጉሥ ታደሰ (ዶ/ር) ምርጫው ሰላማዊ፣ ፍትሓዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ መስራት የሁሉም ወገን ድርሻ መሆኑን ገልጸዋል።

ከሁሉም በላይ ግን በምርጫ ማግሥት የተረጋጋ አገራዊ ሰላም እንዲሰፍን ማድረጉ የቤት ሥራ እና ትኩረት እንደሚፈልግ ተናግረዋል።

በውይይቱ የሀገር አቀፍና ክልላዊ ፓርቲ መሪዎች፣ የሲቪክ ማኅበራት ተወካዮች፣ የዩኒቨርሲቲ መምህራን፣ ሰራተኞችና ተማሪዎች፣ የደብረብርሃን ከተማ ነዋሪዎች እንዲሁም በሕዝብ ዘንድ ተፅዕኖ ፈጣሪና ተሰሚ ናቸው የሚባሉ ግለሰቦች እየተሳተፉ ይገኛሉ።

(በስንታየሁ አባተ)