ም/ጠ/ሚኒስትሩ የሰላም ስምምነቱ በቀጣናው ላሉ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሄ ስለመኖራቸው ትምህርት ሰጪ ነው አሉ

ኅዳር 21/2015 (ዋልታ) በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል የነበረው ግጭት የኢትዮጵያን የግዛት አንድነት እና ሉዓላዊ ክብር ሙሉ በሙሉ ባከበረ መልኩ እንዲፈታ ስምምነት መደረሱ በቀጣናው ላሉ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሄዎች ስለመኖራቸው ትምህርት ሰጪ አካሄድ መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ገለጹ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት 48ኛው የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት (ኢጋድ) የሚኒስትሮች ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር ነው።

ኢትዮጵያ ፈታኝ ሁኔታ ውስጥ በነበረችበት ወቅት የኢጋድ አባል አገራት የሰጡት ያልተቋረጠ ድጋፍ በኢትዮጵያ ህዝብ ዘንድ ምስጋና የሚያሰጠው ተግባር መሆኑንም ገልጸዋል።

የሰላምና ፀጥታ ጉዳይ ለቀጣናው ትልቅ ፋይዳ እንዳለው የተናገሩት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአየር ንብረት ለውጥ እና እያደረሰ ባለው ተፅዕኖ ዙሪያም ያላቸውን ስጋት ገልጸው ይህን ለመግታትም አባል ሀገራት እና አጋሮች የተቀናጀ ጥረት እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

የኢጋድ ዋና ፀሃፊ ወርቅነህ ገበየሁ (ደ/ር) በበኩላቸው ኢጋድ በቀጣናው ሰላምና መረጋጋት እንዲረጋገጥ አዎንታዊ ሚና እየተጫወተ እንደሆነ ጠቅሰው በቅርቡ በኢትዮጵያ የተደረሰው የሰላም ስምምነትም የዚህ ማሳያ መሆኑን ጠቁመዋል።

ኢጋድ ከዚህ በተጨማሪም የአየር ንብረት ለውጥን፣ ድርቅን፣ ተባይ እና ወቅታዊ የጎርፍ አደጋዎችን ለመከላከል እንዲሁም ለምግብ ዋስትና ያለውን ተግዳሮት ለመቅረፍ ምላሽ ለመስጠት ከአባል ሀገራት ጋር በቅርበት እየሰራ መሆኑንም አብራርተዋል።

የኢጋድ የሚኒስትሮች ምክር ቤት የቀጣናውን ሰላምና ደህንነት፣ የሰብዓዊነት ሪፖርት የሚያዳምጥ ሲሆን በዛሬው እለትም ጋዜጣዊ መግለጫ ይሰጣል ተብሎ እንደሚጠበቅ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።