ባለፈው ዓመት በትራፊክ አደጋ 3 ሺሕ 971 ህይወታቸውን ሲያጡ 10 ሺሕ 325 ሰዎች ለጉዳት መዳረጋቸው ተገለጸ

ኅዳር 22/2015 (ዋልታ) በኢትዮጵያ በ2014 ዓ.ም በመንገድ ትራፊክ አደጋ 3 ሺሕ 971 ህይወታቸውን ያጡ ሲሆን 10 ሺሕ 325 ሰዎች ደግሞ ለከባድና ቀላል የአካል ጉዳት መዳረጋውን የመንገድ ደህንነትና መድህን ፈንድ አገልግሎት አስታውቋል።

በመንገድ ትራፊክ አደጋ ምክንያት የሚደርሰውን የንብረትና የሰው ህይወት መጥፋት ሊቀንሱ በሚችሉ ስትራቴጂዎች ዙርያ ውይይት ተካሂዷል።

መድረኩ በመንገድ ደህንነት ዙርያና የአደጋ መንስኤዎቹን ለመከላከልና ቀድመው እንዳይከሰቱ የመፍትሔ አቅጣጫዎች ላይ የመከረ ሲሆን በዚህም ከተለያዩ ተቋማት የተውጣጡ የመንግስት የስራ ሀላፊዎች ተሳትፈውበታል።

በመድረኩ በትራፊክ አደጋዎች ዙርያ የጥናት ፅሁፍ የቀረበ ሲሆን በዚህም ባሳለፍነው አመት ብቻ 3

ሺሕ 971 ሰዎች ህይወታቸውን ያጡ ሲሆን 10 ሺሕ 325 ሰዎች ደግሞ ለከባድና ቀላል የአካል ጉዳት እንደተዳረጉ ተገልጿል።

እንዲሁም ግምቱ ወደ 13 ቢሊየን ብር የሚደርስ የንብረት ውድመት እንደደረሰ ተነስቷል።

በዚህም እየደረሰ የሚገኘውን አደጋ ለመቀነስ የኢንሹራንስ ድርጅቶች በመንገድ ደህንነት ስራ ላይ ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑ እና አደጋዎች ሊያስከትሉ የሚችሉ ተግባራትን ለመቅረፍ በአሽከርካሪ ተቋማት ላይ የአሰልጣኞች ስልጠና መሰጠት እንዳለበት በጋራ ውይይቱ ላይ ተገልጿል።

በግዛቸው ይገረሙ