ሐምሌ 4/2015 (ዋልታ) የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ መሀመድ የተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ አደጋን ለመከላከል በተዘጋጀ እቅድ ላይ ከተለያዩ መንግስታዊ ካልሆኑ የልማት ድርጅቶች ጋር ተወያይተዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ በውይይቱ ላይ እንደተናገሩት በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ የሚከሰቱ አደጋዎችን ከመከላከል አንፃር መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ተሳትፎ አስፈላጊ ነው።
ዕቅዱም የክልሉን ፍላጎትና ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ጉዳዮች በጥልቀት በመገምገም እንዲሁም ወደፊት ሊፈጠሩ የሚችሉ ዕድሎችንና ተግዳሮቶችን በመገምገም ላይ የተመሰረተ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡
በመሆኑም ለዕቅዱ ተግባራዊነት ባለድርሻ አካላት በተለይም የመንግስት አካላት እና የልማት አጋሮች ድርጅቶች፣ ከሲቪክ ማህበራት እና ከግሉ ዘርፍ የተቀናጀ ጥረት እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።
በውይይቱ ላይ በኢትዮጵያ የስዊድን አምባሳደር ሀንስ ሄንሪክ ልንድኩዊስት፣ በአሜሪካ የተራድኦ ድርጅት (ዩ.ኤስ.ኤድ) ሚሽን ዳይሬክተር ቲሞቲ ስቴንን ጨምሮ ሌሎች የተራድኦ ድርጅት አመራሮች ተገኝተዋል፡፡
በመድረኩ ላይ ለአምስት ዓመታት በተዘጋጀ እቅድ ላይ ሰፊ ውይይት ተደርጓል፡፡
ተስፋዬ ኃይሉ (ከሀረር ቅርንጫፍ)