በጅግጅጋ ከተማ በእሳት አደጋ ንብረታቸው የተጎዳባቸው ወገኖችን መልሶ ለማቋቋም የሀብት ማሰባሰብ ስራ ተጀመረ

ሐምሌ 4/2015 (ዋልታ) በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማ ተከስቶ በነበረው የእሳት አደጋ ንብረታቸው የተጎዳባቸው ወገኖችን መልሶ ለማቋቋም የሀብት ማሰባሰብ ስራ መጀመሩን የክልሉ መንግስት አስታወቀ።

የክልሉ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አብዲቃድር ረሺድ ባለፈው አርብ ምሽት በከተማው የገበያ ማዕከል ተከስቶ በነበረው የእሳት አደጋ የሚተዳደሩባቸው የንግድ ተቋማት የተጎዳባቸው ወገኖች ለችግር መጋለጣቸውን ገልጸዋል።

ተጎጂዎቹን መልሶ ለማቋቋም ሀብት የማሰባሰብ ስራ መጀመሩንና ይህንንም በማስተባበር የሚያስፈጽም ከመንግስት፣ ከአገር ሽማግሌዎች እና ከንግዱ ማህበረሰብ የተውጣጡ አካላትን ያካተተ ኮሚቴ መቋቋሙን አመልክተዋል።

“ደሀብሺል” የተሰኘ የንግድ ድርጅት 20 ሚሊየን ብር ድጋፍ ለማድረግ ቃል መግባቱንም ጠቁመዋል።

ኮሚቴው ሌሎች ኢትዮጵያዊያን እና ለጋሽ አካላት ድጋፍ የሚያደርጉበት የሀብት ማሰባሰቢያ የባንክ ሂሳብ ቁጥር ለመክፈት እንቅስቃሴ መጀመሩንም መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

በጅግጅጋ ከተማ የገበያ ማዕከል ተከስቶ በነበረው የእሳት አደጋ ከ900 የሚበልጡ ሱቆችና መጋዘኖች በቃጠሎ ጉዳት ደርሶባቸዋልም ነው የተባለው።

#በአንድ_ጀምበር_500_ሚሊየን_ችግኝ
#ነገን_ዛሬ_እንትከል
#ዐሻራ_ለትውልድ
#ይህ_የኢትዮጵያ_ጉዳይ_ነው!