ሴቶች የተሻለ ቦታ እንዲደርሱ በትምህርት ቤቶች ውስጥ ምቹ ሁኔታን መፍጠር እንደሚገባ ፕሬዝዳንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴ ተናገሩ

የካቲት 26/2013(ዋልታ)– ፕሬዝዳንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴ እና የትምህርት ሚኒስትሩ ጌታሁን መኩሪያ (ፒኤችዲ) የሴቶች ቀንን ምክንያት በማድረግ ቱሉ ዲምቱ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤትን ጎብኝተዋል።

በጉብኝቱም በትምህርት ቤት ውስጥ እየተደረገ ስላለው የሴት ተማሪዎች ድጋፍ እና በትምህርት ቤት ውስጥ ስላለው የትምህርት አሰጣጥ ሂደት ገለፃ ተደርጓል።

በትምህርት ቤት ውስጥ ያሉት የልዩ ፍላጎት እና የስነ ልቦና ድጋፍ መስጫ ክፍሎች ጉብኝት የተደረገ ሲሆን በባለሙያዎችም ስለሚሰጠው አገልግሎት ማብራሪያ ቀርቧል።

ፕሬዝዳንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴ በትምህርት ቤት ውስጥ የስርዓተ ፆታ ክበብ በማቋቋም ጥቃቶችን ለመከላከል እየተሰራ ያለው ስራ አበረታች መሆኑን ገልፀው ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አሳስበዋል።

ትምህርት ቤቱ ለሴት ተማሪዎች ምቹ ሁኔታን የፈጠረ በመሆኑ ሌሎች ትምህርት ቤቶችም ይህን አርያ ሊከተሉ እንደሚገባ ፕሬዝዳንቷ ጠቁመዋል።

ሴት ልጅ የተሻለ ቦታ እንድትደርስ የሁሉም ድጋፍ ያስፈልጋል ያሉት ፕሬዝዳንቷ የነገ የበለፀገች ኢትዮጵያን ለመገንባት የሴቶች ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።

ሴቶች የተሻለ ቦታ እንዲደርሱ በትምህርት ቤቶች ውስጥ ምቹ ሁኔታን መፍጠር እንደሚገባ  ገልፀው ተማሪዎች ትምህርታቸው ላይ እንዲያተኩሩ መልዕክት ማስተላለፋቸውን ከትምህርት ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡