በሰላም እና ግጭት አስተዳደር የትምህርት ዘርፍ ትምህርት መስጠት መጀመሩ ተገለፀ

ግንቦት 07/2013(ዋልታ) – የሰላም ማስከበር ማዕከል የአለም አቀፍ ሰላም ማስከበር ኢኒስቲቲውት በሰላም እና ግጭት አስተዳደር የትምህርት ዘርፍ ትምህርት መስጠት መጀመሩን አስታወቀ።
በኢፌዴሪ መከላከያ የግንባታ ስራዎች ዋና አስተባባሪ ሌተናል ጀነራል ባጫ ደበሌ እንደገለፁት ፣ አሰራርን በማዘመን በዲሲፕሊን የታነፀ ፣ በዕውቀት የዳበረ ፣ በቴክኖሎጂ የጎለበተ እና በሰላም ማስከበር ግዳጅ ላይ ብቁ የሆነ ሰራዊት ለመፍጠር ይህ የትምህርት ዘርፍ መጀመሩ የሚበረታታ ነው ብለዋል።
”የሀገር ክብር ሳይረጋገጥ የግል ጥቅምም ሆነ መብት ማስጠበቅ አይቻልም ፣ ሰራዊቱም በሚሰማራበት የሰላም ማስከበር ግዳጅ ላይ ከምን ጊዜ በላይ የሀገሩ አምባሳደር በመሆን ከተልኮው ጎን ለጎን የሀገሩን እና የተቋሙን መልካም ገፅታዎች ለአለም ማህበረሰብ ሊያሳውቅ ይገባል” ብለዋል።
የመከላከያ ዋር ኮሌጅ ዋና አዛዥ ሜጀር ጀነራል ሀብታሙ ጥላሁን በበኩላቸው ፣ ይህ የትምህርት ዘርፍ መሰጠት መጀመሩ ተቋማችንን በአለም የሰላም ማስከበር ግዳጅ ላይ የጎለበተ የሚያደርግ እና ሰራዊቱንም ወቅቱ ከሚጠይቀው ቀልጣፋና በዕውቀት የተደገፈ ስራ እንዲሰራ ያደርገዋል ብለዋል ።
በማዕከሉ የተሰሩ የልማት ስራዎች በውይይቱ ላይ በተሳተፉ ከፍተኛ የሰራዊቱ አመራሮች መጎብኘታቸውን ከመከላከያ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል ።