የመርካቶ ዘመናዊ የከተማ አውቶቡስ ተርሚናል በይፋ ተመረቀ

ግንቦት 07/2013 (ዋልታ) – ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ በ200 ሚሊዮን ብር ወጪ የተገነባውን መርካቶ ዘመናዊ የከተማ አውቶቡስ ተርሚናል በይፋ መርቀው ስራ አስጀመሩ።
ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ በመርካቶ የከተማ አውቶቡስ ተርሚናል የምርቃት ስነስርዓት እንደገለፁት በከተማዋ የህዝብ ትራንስፖርት አቅርቦት ችግሮችን ከማቃለል ባለፈ ለትራንስፖርት ዘርፍ የመሰረተ ልማት ችግሮች እንዲፈቱ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
ከተማ አስተዳደሩ መፈታት አለባቸው ብሎ በትኩረት እየሰራባቸው ካሉ ጉዳዮች የትራንስፖርት ችግርን መፍታት አንዱ ነው ያሉት ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ለትራንስፖር ዘርፉ መሰረተ ልማት ማሟላት፣ ስምሪቱን በቴክኖሎጂ ማዘመንና ዘመናዊ አውቶቡሶችን ማስገባት ስራዎች እየተሰሩ ነው ብለዋል።
በተለይ በከተማዋ የሚስተዋለውን የተሽከርካሪ ፓርኪንግ ችግር ለመቅረፍ በመስቀል አደባባይ፣ በታላቁ ቤተመንግሥት እና በሌሎች ግንባታዎች ተጨማሪ የተሽከርካሪ ፓርኪንግ ቦታዎች በመገንባት ላይ መሆኑን ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ገልጸዋል ።
ይህ ዛሬ የተመረቀው የመርካቶ የአውቶቢስ ተርሚናል መርካቶና አካባቢው ያለውን ከፍተኛ የህዝብ እንቅስቃሴ የትራንስፖርት እጥረት መቅረፍና ምቾትን ይጨምራል ብለዋል ።
ፕሮጀክቶችን በተያዘላቸው እቅድ መሠረት በመተግበራችን አብዛኛዎቹን ማጠናቀቅ ችለናል ብለዋል አዳነች አበቤ ።
የአዲስ አበባ ከተማ ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ ኢ/ር ስጦታው አከለ በበኩላቸው ይህ የከተማ አውቶቡስ ተርሚናል በመርካቶ አካባቢ የሚስተዋለውን የትራንስፖርት መጨናነቅ ለመቀነስ በአንድ ሰዓት 6 ሺህ ፤በቀን ደግሞ እስከ 80 ሺህ የትራንስፖርት ተጠቃሚዎችን አገልግሎት የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል ።
የአዲስ አበባ ፕረስ ሴክረታሪያት መረጃ እንዳመለከተው በ200 ሚሊዮን ብር ወጪ የተገነባው ይህ ዘመናዊ ተርሚናል በአንዴ ለ20 አውቶቡሶች አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሲሆን ብዛታቸው 35 የሚደርሱ የአንበሳ የከተማ አውቶቡስ ድርጅት መስመሮች እና 17 ደግሞ ሸገር የብዙሃን ትራንስፖርት ድርጅት መስመሮች በድምሩ 52 መስመሮች ላይ አገልግሎት መስጠት ያስችላል ተብሏል።