በበልግ ዝናባማ አካባቢዎች ከመደበኛው በታች የአየር ፀባይ ሊዘወተር እንደሚችል ተጠቆ

በመጪው በልግ ወቅት በአብዛኛው የሀገሪቱ ዝናብ ተጠቃሚ አካባቢዎች ላይ መደበኛና ከመደበኛው በታች የአየር ፀባይ ሊዘወተር እንደሚችል የብሔራዊ ሜትሮሎጂ ኤጀንሲ አስታወቀ፡፡

በመጪው የበልግ ወቅት የሰሜን-ምስራቅ የሀገሪቱ አካባቢዎች በአመዛኙ በደረቃማ የአየር ፀባይ ተጽዕኖ ሥር ሊቆዩ እንደሚችሉ ኤጀንሲው ለዋልታ የላከው መረጃ አመላክቷል።

በልግ ዋነኛ የዝናብ ወቅታቸዉ የሆኑት የደቡብና ደቡብ ምስራቅ አካባቢዎች መደበኛና ከመደበኛ በታች ዝናብ ሊያገኙ እንደሚችሉ ይጠበቃል ተብሏል፡፡

በሌላ በኩል የምእራብ አጋማሽ የሀገሪቱ አካባቢዎች መደበኛና ከመደበኛ በላይ፣ እንዲሁም የመካከለኛውና የደቡብ ደጋማ አካባቢዎችን ጨምሮ ወደ መደበኛ ያደላ ዝናብ ሊያገኙ እንደሚችሉ በትንበው ተመላክቷል፡፡

በአንዳንድ የሰሜን ምዕራብ፣ የሰሜን ምስራቅ፣ የምስራቅ፣ የደቡብና ደቡብ ምስራቅ ቆላማ የሀገሪቱ አከባቢዎች ላይ የቀኑ ከፍተኛ የሙቀት መጠን ከመደበኛው በላይ ሊመዘገብ እንደሚችልም ተጠቁሟል፡፡

በተጨማሪ በልግ የዝናብ ወቅታቸው የሆኑት የአገሪቱ አካባቢዎች ላይ በመጪው በልግ ወቅት መደበኛና ወደ መደበኛው በታች ያደላ ዝናብ ሊኖራቸው እንደሚችል የኤጀንሲ ትንበያ ያመላክታል፡፡

በመሆኑም ኤጀንሲው አርሶ አደሩ፣ አርብቶ አደሩና ከፊል አርብቶአደሩ በተወሰነ መልኩ አነስተኛ ቢሆንም፣ የሚገኘውን እርጥበት በአግባቡ በመሰብሰብ እንዲጠቀምበት ምክር ሀሳብ ሰጥቷል።

በዛሬው ዕለት በአዳማ ከተማ የበጋ ወቅት የአየር ጠባይ ግምገማና በሚቀጥለው የበልግ ወቅት በሚጠበቀው የወቅት አየር ጠባይ ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት እየተካሄደ ነው፡፡