የካቲት 21/2013 (ዋልታ) በታላቁ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ የምሁራንን ተሳትፎ የሚያስተባብር ፎረም ለመመሰረት የሚያግዝ ጊዜያዊ ኮሚቴም ተደራጅቷል፡፡
ጊዜያዊ ኮሚቴዉ የፎረሙን አደረጃጀት አስመልክቶ ጥናት በማድረግ የመቋቋሚያ ምክረ-ሀሳብ የሚያቀርብ ሲሆን በአጭር ጊዜ ዉስጥ ፎረሙ ይመሰረታል ተብሏል፡፡
ጊዜያዊ ኮሚቴዉ በህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ጸሀፊነት ከሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር አስተባባሪነት፤ ዉሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር፤ እንዲሁም ዩኒቨርስቲዎችንና የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎችን አባላት በማድረግ ተመስርቷል፡፡
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ፕ/ር አፈወርቅ ካሱ በህዳሴዉ ግድብ ዙርያ ምሁራንን የሚያስተባብር አደረጃጀት እንዲፈጠር የረጅም ጊዜ ጥያቄዎች ነበሩ ያሉ ሲሆን የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴርም ዩኒቨርስቲዎችን በማስተባበር በፎረሙ ምስረታ ሂደት ድጋፍ እንደሚያደርግ ተናግረዋል፡፡
በምስረታ ሂደቱ ዙርያ በተደረገዉ ዉይይት አስተያየት የሰጡ የጉባኤዉ ተሳታፊዎች የሚመሰረተዉ ፎረም በተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀም፤ በግድቡ አሞላልና በአባይ ጉዳይ እየታተሙ ያሉ የተሳሳቱ መረጃዎችን ጨምሮ በሌሎች ሙያዊ ጉዳዮች ላይ በማተኮር ለመንግስትና ዓለማቀፉ ማህበረሰብ በአባይ ጉዳይ የሚሰራ ሊሆን ይገባዋል ማለታቸውን ከሚንስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡