በትግራይ ክልል ከ4 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ ለሆኑ ዜጎች ምግብና ምግብ ነክ ሰብዓዊ ድጋፍ ቀርቧል- የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

አምባሳደር ዲና ሙፍቲ

መጋቢት 7/2013 (ዋልታ) – በትግራይ ክልል ከ4 ነጥብ 2 ሚሊየን በላይ ለሆኑ ዜጎች ምግብና ምግብ ነክ ሰብዓዊ ድጋፍ መቅረቡን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።

የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ የወቅቱን አበይት ሳምንታዊ ክንውኖች በተመለከተ መግለጫ ሰጥተዋል።

በሳምንቱ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ከተለያዩ አገሮች አቻቸውና አምባሳደሮች ጋር መወያየታቸውን፣ በአዲስ አበባ የሚገኙ የተለያዩ አገሮች አምባደሮች በትግራይ ክልል በአካል ተገኝተው ሁኔታውን መመልከታቸውንና እርዳታ ለማድረግ አዎንታዊ ምላሽ መስጠታቸውን አስታውሰዋል።

በክልሉ ባለው ሰብዓዊ እርዳታና ተያያዥ ጉዳዮችም በአገር ውስጥ ካሉ ኤምባሲ ዲፕሎማቶች በተጨማሪ በተለያዩ አገሮች የሚገኙ አምባሳደሮች ለሚመለከታቸው አገሮች መንግስታት የማስረዳት ዲፕሎማሲ ስራዎች ማከናወናቸውን ተናግረዋል።

በትግራይ ክልል መልሶ ግንባታ እየተካሄደ መሆኑን፣ በክልሉ 4 ነጥብ 2 ሚየሊን ዜጎች ምግብና ምግብ ነክ እርዳታ ደርሷል።

በቀጣይ ምዕራፍ ድጋፍ የሚሹ ዜጎችን የመለየት ዳሰሳ እየተካሄደ መሆኑም ተገልጿል።

በዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ ከተለያዩ አገሮች ዜጎች እየመለሱ መሆኑን፣ በየመን ኤደን የሚገኙ ዜጎች ውስጥ ከ150 በላይ የሚሆኑ ዛሬ እንደሚመለሱ አምባሳደር ዲና ገልፀዋል።

በየመን ሰንዓ እስር ቤት በደረሰው የእሳት አደጋም ህይወታቸው ካለፉት 43 ሰዎች መካከል ኢትዮጵያን እንዳሉበት ገልፀዋል።

ከሳዑዲ አረቢያ ጂዳ ብቻ 888 ዜግች በሳምንቱ መመለሳቸውን አስታውሰዋል።

በአሜሪካና አውሮፓ አገሮች ኢትዮጵያዊያን ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ወግነው ያካሄዱት የድጋፍ ሰልፍም የሳምንቱ አበረታች ክስተት እንደነበር በመግለጽ ምስጋና ማቅረባቸውን የኢዜአ ዘገባ ያመለክታል።