በመተከል ዞን በሰላማዊ መንገድ እጃቸውን ለሰጡ ታጣቂዎች የተሃድሶ ስልጠና ሊሰጥ ነው

መጋቢት 07/2013 (ዋልታ) – በመተከል ዞን እየተወሰደ ባለው የህግ ማስከበር እርምጃ በሰላማዊ መንገድ እጃቸውን ለሰጡ ታጣቂዎች የተሃድሶ ስልጠና ለመስጠት ዝግጅቱ መጠናቀቁን የምዕራብ ዕዝ ምክትል አዛዥና የግብረ ሃይሉ አባል ብርጋዴር ጄኔራል አለማየሁ ወልዴ ገለጹ።

በዞኑ እስካሁን 3 ሺህ 230 የታጣቂ ቡድኑ አባላት በሰላማዊ መንገድ እጃቸውን መስጠታቸውም ታውቋል።

በመተከል ዞን የተቋቋመው የተቀናጀ ግብረ ሃይል ከግልገል በለስ ከተማ ነዋሪዎች ጋር በወቅታዊ ጉዳይ ዙሪያ ውይይት አድርጓል።

የምዕራብ ዕዝ ምክትል አዛዥና የግብረ ሃይሉ አባል ብርጋዴር ጄኔራል አለማየሁ ወልዴ እንደገለጹት በህግ ማስከበር ዘመቻው በሰላማዊ መንገድ እጃቸውን ለሰጡ ታጣቂዎች የተሃድሶ ስልጠና ለመስጠት ዝግጅት ተደርጓል።

እስካሁን 3 ሺህ 230 የታጣቂ ቡድኑ አባላት በሰላማዊ መንገድ እጃቸውን መስጠታቸውን አስታውሰው፤ ግብረ ሃይሉ ስልጠና ሊሰጣቸው መሆኑን ገልጸዋል።

በተሃድሶ ስልጠናው ታጣቂዎቹ ትክክለኛ የሰላም አስተሳሰብ እንዲይዙ በማድረግ በአካባቢው ሰላም፣ ልማት፣ ኢኮኖሚያዊ እድገትና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ የበኩላቸውን እስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ ለማድርግ መሆኑን ተናግረዋል።

የታጠቁ ሃይሎችን በተመለከት  በተለያዩ በማህበራዊ ሚዲያዎች እየተሰራጨ ያለው መረጃ የተሳሰተ መሆኑንም አብራርተዋል።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ  ክልል የሰላም ግንባታና ፀጥታ ቢሮ ሃላፊ አቶ አብዮት አልቦሮ በበኩላቸው የከተማዋ ነዋሪዎች የፖለቲካ ቁማርተኞች በማህበራዊ ሚዲያ በሚያሰራጩት የተሳሳተ መረጃ መደናገር እንደሌለባቸው ገልፀው፤ አንድነታቸውን በማጠናከር የአከባቢያቸውን ሰላም እንዲጠብቁ ማሳሰባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።