በአክሱም ከተማ የተሻለ ሰላምና መረጋጋት ቢኖርም አልፎ አልፎ የስርቆትና የዘረፋ ወንጀሎች እንዳሉ ነዋሪዎች ገለጹ

መጋቢት 16/2013 (ዋልታ) – በትግራይ ክልል አክሱም ከተማ የተሻለ ሰላምና መረጋጋት ቢኖርም፤ አልፎ አልፎ የስርቆትና የዘረፋ ወንጀሎች መኖራቸውን የከተማዋ ነዋሪዎች ገለጹ።
የከተማዋ የንግድ እንቅስቃሴም በየጊዜው መሻሻል እያሳየ መሆኑንም ተናግረዋል።
በትግራይ ክልል የተካሄደው የህግ ማስከበር ዘመቻ ከተጠናቀቀ በኋላ አክሱም ከተማ ወደ ሰላማዊ እንቅስቃሴዋ ተመልሳ ነዋሪዎች ወደ መደበኛ ስራቸው ተመልሰዋል።
ሆኖም አልፎ አልፎ የስርቆትና የዘረፋ ወንጀሎች እየተፈፀሙ መሆኑን ኢዜአ ያነጋገራቸው የከተማዋ ነዋሪዎች ገልጸዋል።
“የተሰማራው የፀጥታ ሃይል ጥበቃ እያደረገና ነዋሪውን ለማገዝ የተቻለውን ሁሉ ጥረት እያደረገ ነው” ያሉት ነዋሪዎቹ፤ በአሳቻ ስፍራዎች ዘረፋ የሚፈፅሙ ወንጀለኞች መኖራቸውን ጠቁመዋል።
የከተማዋ የንግድ እንቅስቃሴም በየጊዜው መሻሻል እያሳየ መሆኑን ጠቅሰው፤ ሱቆች፣ መደብሮችና ሌሎች የግብይት ስፍራዎች ስራ መጀመራቸውን ተናግረዋል።
የከተማው ነዋሪ መደበኛ እንቅስቃሴ እና ግብይት በጥሩ ሁኔታ ቢቀጥልም የፀጥታ ሃይል በማይኖርባቸው አካባቢዎች ስርቆትና ዘረፋ እየተፈፀመ መሆኑን ተናግረዋል።
በመሆኑም ወንጀለኞችን ለመቆጣጠር ህዝቡ ከፀጥታ ሃይሉ ጋር ያለውን ትብብር በማጠናከር መስራት እንደሚጠበቅበት ነዋሪዎቹ አስገንዝበዋል።
የአክሱም ከተማ ጊዜያዊ አስተዳደር የሰላምና የጸጥታ ሃላፊ አቶ አስገዶም ስዩም በበኩላቸው “አክሱም ሰላማዊና የተረጋጋች ከተማ ሆናለች፣ የንግድ እንቅስቃሴውም በጥሩ ሁኔታ ላይ ይገኛል” ብለዋል።
ለከተማዋ ሰላምና መረጋጋት ማህበረሰቡ ከጸጥታ ሃይሎች ጋር በመተባበር የድርሻውን እየተወጣ መሆኑንም አረጋግጠዋል።
በከተማዋ ጁንታው ከእስር በለቀቃቸው ግለሰቦች አልፎ አልፎ የሚስተዋሉ የስርቆትና የዘረፋ ወንጀሎች መኖራቸውን ገልጸው፤ ይህንን ለማስቀረት አደረጃጀት በመፍጠር የተጠናከረ ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ከህብረተሰቡ፣ ከአገር መከላከያ ሰራዊት እና ከፌዴራል ፖሊስ ጋር በቅንጅት እየተሰራ እንደሆነና ይህም እንደሚቀጥል አቶ አስገዶም ተናግረዋል።
ወንጀለኞቹን በቁጥጥር ስር በማዋል ወደ ህግ ለማቅረብ ማህበረሰቡ ከጊዜያዊ አስተዳደሩና የፀጥታ ሃይሉ ጋር ያለውን ትብብር አጠናክሮ እንዲቀጥል ሃላፊው ጠይቀዋል።