በኢሉባቦር ዞን በፍቃደኝነት መከላከያን ለመቀላቀል የወሰኑ ወጣቶች ተሸኙ

ኢሉባቦር ዞን ወጣቶች

ሐምሌ 19/2013 (ዋልታ) – በኢሉባቦር ዞን በፍቃደኝነት መከላከያ ሠራዊቱን ለመቀላቀል  ለወሰኑ ወጣቶች ሽኝት ተደረገላቸው።

የመከላከያ ሠራዊቱን ለመቀላቀል ተመዝግበው ሽኝት የተደረገላቸው ወጣቶችም መንግሥት የሀገርን ሉዓላዊነት ለማስከበር ያደረገውን ጥሪ ተቀብለው መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።

ወጣት መልካሙ ድሪባ “አባቶች በጀግንነት ሉዓላዊነቷን ጠብቀው ለዛሬ ያደረሷትንና ያስረከቡንን ሀገር ሰላም ለማስከበር መንግስት ያደረገውን ጥሪ በመቀበል በፈቃዴ ተነስቻለሁ” ብሏል።

ወጣቱ አክለውም “የሀገርን ጥሪ ተቀብሎ ሀገር በፈለገችው መስክ ለማገልገል መቆም  እድለኛነት ነው” ብሏል።

ሱልጣን መሐመድ በበኩሉ “አባቶች በአሸናፊነት  ያቆዩልንን  ሉዓላዊት ሀገራችን በኛ ዘመን ለጠላት አትንበረከክም፤ እኛም የኛን ድርሻ ለመወጣትና ሀገራችንን ከመፍረስ ለመታደግ ተነስተናል” ብሏል።

ትላንት በተዘጋጀው የሽኝት ስነ ስርዓቱ ላይ ለወጣቶቹ መልዕክት ያስተላለፉት የዞኑ ምክትል ዋና አስተዳዳሪ አቶ መኮንን ባይሳ “አባቶች በደምና በአጥንታቸው የገነቧትንናያስረከቧትን ሀገር ዛሬ ደግሞ ሉዓላዊነቷ ሳይነካ በናንተ ውድ ልጆቿ ተከበራ ትቀጥላለች” ብለዋል።

“እናት ሀገራችሁ ዛሬ በእናንተ ስለምትኮራባችሁ እንኳን ደስ አላችሁ” ሲሉ ለወጣቶቹ አድናቆትን ችረዋል።

እንደ ኢዜአ ዘገባ በሽኝት ስነ ሥርዓቱ ላይ የኃይማኖት አባቶችና አባ ገዳዎች ተገኝተው ወጣቶቹን መርቀዋል።