በኢትዮጵያ የዲጂታል ኢኮኖሚ መሰረት ለመጣል በትኩረት እየተሰራ መሆኑ ተገለፀ

ጥር 6/2014 (ዋልታ) በኢትዮጵያ የዲጂታል ኢኮኖሚ መሰረት ለመጣል በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ገለፀ፡፡

የሚኒስቴሩ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ በዓለም ባንከ የኢትዮጵያን የዲጂታል ፋውንዴሽን ፕሮጀክት በበላይነት ከሚከታተሉት የደርጅቱ የአይ ሲ ቲ ፖሊሲ መሪ ቲም ሜሊ (ዶ/ር) ጋር በፕሮጀክቱ አፈፃፀም ዙሪያ መክረዋል፡፡

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በበላይነት የሚመራው የዲጂታል ፋውንዴሽን ፕሮጀክት የቅድመ ዝግጅት ስራዎች በተያዘላቸው እቅድ መሰረት እየተከናወኑ መሆናቸውን ሚኒስትር ዴኤታዋ አብራርተዋል፡፡

ባለፉት ስድስት ወራት የተከናወኑ ስራዎችን ያብራሩት ሚኒስትር ዴኤታዋ ፕሮጀክቱ የታለመለትን ግብ እንዲመታና በኢትዮጵያ የዲጂታል ኢኮኖሚ መሰረት ለመጣል በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በዓለም ባንክ የአይሲቲ ፖሊሲ መሪ እና በባንኩ የኢትዮጵያን የዲጂታል ፋውንዴሽን ፕሮጀክት የሚከታተሉት ቲም ኬሊ (ዶ/ር) የዲጂታል ዘርፉን የሚደግፉ ቀጣይ ቀጣናዊ ፕሮጀክቶች መኖራቸውን አንስተዋል፡፡

ኢትዮጵያም በእነዚህ ፕሮጀክቶች ተጠቃሚ መሆን እንደምትፈልግ ሚኒስትር ዴኤታዋ አብራርተውላቸዋል፡፡

በቀጣይ ይፋ የሚደረገው አንዱ ቀጣናዊ ፕሮጀክት ኢትዮጵያን፣ ሱዳንን፣ ደቡብ ሱዳንንና ሶማሊያን ተጠቃሚ ማድረግ የሚችል ነው ማለታቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡