በጎንደር የጥምቀት በዓል በሰላም እንዲከበር ኅብረተሰቡን ያሳተፈ የፀጥታ ስራ እየተከናወነ መሆኑ ተገለፀ

ጥር 6/2014 (ዋልታ) በጎንደር ከተማ የጥምቀት በዓል በሰለም እንዲከበር ኅብረተሰቡን ያሳተፈ የፀጥታ ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ የዞኑ ፖሊስ መምሪያ አስታወቀ።
የጥምቀት በዓል በዩኒስኮ ከማይዳሰሱ ቅርሶቹ መካከል አንዱ ሲሆን ይህ በዓል በጎንደር ከተማ በሰላም እንዲከበር በየአካባቢው የጥበቃ ሁኔታና የቅድመ ዝግጅት ስራው ተጠናክሮ መቀጠሉ ተጠቁሟል።
ለዚህም ኅብረተሰቡን ያሳተፉ አደረጃጀቶችን ፈጥሮ እንቅስቃሴ እያደረገ እንደሚገኝ ነው የፖሊስ መምሪያው ያስታወቀው።
የጎንደር ከተማ መደበኛ ፖሊስ፣ የአድማ መከላከል ፖሊስ፣ ሚሊሻና የግል ታጣቂዎች የብሎክ አደረጃጀቶችን መሰረት በማድረግ አካባቢውን የመጠበቅ ተግባር እየሰራ እንደሚገኝም ተገልጿል።
የጥምቀት በዓል በሰላም እንዲጠናቀቅ ከመቼውም ጊዜ በላይ አካባቢያቸውን እንዲጠብቁና ሁሉም ኅብረተሰብ “የከተማዋ ሰላም የኔ ሰላም ነው” ብሎ የድርሻውን እንዲወጣ የጎንደር ከተማ ፖሊስ ጥሪ ማቅረቡን ከአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።