በኦሮሚያ ክልል ኢንተርፕራይዞችን ወደ መካከለኛ ባለሃብትነት የማሸጋገር ሥነሥርዓት እየተካሄደ ነው

መጋቢት 25/2014 (ዋልታ) በኦሮሚያ ክልል በጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ተደራጅተው ውጤታማ የሆኑ 740 ኢንተርፕራይዞችን ወደ መካከለኛ ባለሃብትነት የማሸጋገር ሥነሥርዓት በአዳማ ከተማ እየተካሄደ ነው።
በሥነሥርዓቱ ላይ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳን ጨምሮ የፌዴራልና የክልሉ ከፍተኛ መንግሥት ሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
በክልሉ ወደ መካከለኛ ባለሃብትነት እየተሻጋገሩ ያሉት ኢንተርፕራይዞቹ በጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት ተደራጅተው በተሰማሩበት የሥራ ዘርፍ ስኬታማ መሆናቸው ተመልክቷል።
እንደኢዜአ ዘገባ ኢንተርፕራይዞቹ በመንግሥት የተፈጠረላቸውን ዕድል ተጠቅመው ባከናወኑት ውጤታማ ሥራ ከ2 እስከ 12 ሚሊዮን ብር የሚገመት ሀብት ያፈሩ እንደሆኑም ተገልጿል።
ከዚህም ባሻገር ከራሳቸው አልፈው በየአካባቢያቸው ለሚገኙ ከ12 ሺሕ ለሚበልጡ ሥራ አጥ ወገኖች የሥራ ዕድል እንደፈጠሩም በሥነሥርዓቱ ላይ ተነግሯል።
በተጨማሪም በጥቃቅንና አነስተኛ ተደራጅተው በተሰማሩበት የሥራ ዘርፍ ውጤታማ ለሆኑ 389 ኢንተርፕራይዞች በሥነሥርዓቱ ላይ ዕውቅና እንደሚሰጣቸው ከወጣው መርሃ ግብር ለማወቅ ተችሏል።