የዩክሬን ምጣኔ ሀብት 40 በመቶ እንደሚቀንስ ተገለጸ

መጋቢት 25/2014 (ዋልታ) ሩሲያ እና ዩክሬን መካከል በተከሰተው ጦርነት ምክንያት የዩክሬን ምጣኔ ሀብቷ በዚህ ሩብ ዓመት 16 በመቶ የቀነሰ ሲሆን በፈረንጆቹ 2022 ደግሞ 40 በመቶ እንደሚቀንስ የሀገሪቱ የኢኮኖሚ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
ሚኒስቴሩ እንደገለጸው በርቀት መስራት ያልተቻለባቸው ቦታዎች ይበልጥ ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡
በሩሲያ ላይ የተጣሉ ማዕቀቦች የአሜሪካን ዶላር የበላይነት ሊቀንሱ እንደሚችሉ ዓለም ዐቀፉ የገንዘብ ተቋም አይ ኤም ኤፍ ማሳሰቡ ይታወሳል፡፡
የዩክሬን ምክትል የኢኮኖሚ ሚኒስትር ዴኒስ ኩዲን የአየር እና ውቅያኖስ አገልግሎት ዘርፎች ክፉኛ መጎዳታቸውን መግለፃቸውን ሲጂቲኤን አስነብቧል።
ባለፉት 10 ቀናት የአገሪቱ ምጣኔ ሀብት ማገገም መጀመሩን ገልጸው ደኅንነቱ በተጠበቀ ክልል ውስጥ የንግድ ድርጅቶች ሥራቸው ስለመቀጠላቸውና አርሶ አደሮች ዘር መዝራት መጀመራቸውን ጠቁመዋል።
ሩሲያ በዩክሬን ላይ ልዩ ወታደራዊ ዘመቻ መክፈቷን ተከትሎ በሩሲያ፣ አውሮፓ እና አሜሪካ መካከል ያለው ግንኙነት ውጥረት ውስጥ ገብቷል፡፡
በምዕራባዊያን ተጽእኖ አማካኝነት የተመድ ጠቅላላ ጉባኤ ባደረገው ስብሰባ አብዛኞቹ ሀገራት የሩሲያን ወታደራዊ ዘመቻ አውግዘዋል፤ የተወሰኑ ሀገራት ሩሲያን እንደማያወግዙ ጠቅሰው የተቃወሙም ነበሩ፡፡
ምዕራባዊያን ሀገራት ሩሲያን እንዲያወግዙ ዲፕሎማሲያዊ እንቅስቃሴ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡
ሩሲያ እና ዩክሬን ችግሩን ለመፍታት በቱርክ አመቻችነት ድርድር መጀመራቸው ይታወሳል፡፡