በክልሉ የሰላም ጥሪውን ተከትሎ ከ5 ሺሕ በላይ አካላት ወደ ሰላማዊ መንገድ መመለሳቸው ተገለጸ


ታኅሣሥ 13/2016 (አዲስ ዋልታ) መንግሥት በአማራ ክልል ያደረገውን የሰላም ጥሪ ተከትሎ ከ5 ሺሕ በላይ አካላት ወደ ሰላማዊ መንገድ መመለሳቸው ተገለጸ።

በክልሉ የመንግስትን ጥሪ ተቀብለው በርካታ አካላት ወደ ሰላማዊ ህይወታቸው እየተመለሱ እንደሆኑና በመመለስ ላይ የሚገኙ አካላትም የሰላም አምባሳደር እንዲሆኑ የማድረግ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል በብልጽግና ፓርቲ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ይርጋ ሲሳይ ገልጸዋል።

እስከ ታኅሣሥ 11 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ ከ5 ሺሕ በላይ አካላት ጥሪውን ተቀብለው ወደ ሰላማዊ መንገድ ተመልሰዋል ያሉት ኃላፊው በመመለስ ላይ ለሚገኙ አካላት የተሃድሶ ስልጠና እንደሚሰጥና ህዝቡን ይቅርታ እየጠየቁ ወደ ማህበረሰቡ እንደሚቀላቀሉ ተናግረዋል።

የክልሉ መንግሥት ያቀረበው የሰላም ጥሪም በአጭር ጊዜ ውጤታማ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የሰላም ጥሪውን ተከትሎ የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች የጽንፈኛው ቡድን አባላት ከተደበቁበት ወጥተው ለሰላም ጥሪው ምላሽ እንዲሰጡ ኃላፊነት ወስደው በመስራት ላይ እንደሚገኙም ገልጸዋል።

የጽንፈኛ ቡድኑን የተቀላቀሉ ወጣቶች ወደ ሰላማዊ መንገድ እንዲመለሱ የማድረጉ ጉዳይ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ጠቁመዋል።

የምስራቅ ዕዝ ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል መሐመድ ተሰማ በበኩላቸው የክልሉ መንግሥት ያቀረበው የሰላም ጥሪ በርካታ የተደናገሩ አካላት ወደ ሰላም እንዲመለሱ ዕድል መፍጠሩን ተናግረዋል።

የመከላከያ ሰራዊትም የክልሉን የሰላም ጥሪ በማክበር ሥራዎችን እንደሚሰራ ጠቁመው የጽንፈኛው ቡድን አባላት የሰላም ጥሪውን መቀበላቸው ተጠቃሚ እንደሚያደርጋቸው አስገንዝበዋል።

የተሰጠውን የሰላም ጥሪ በማይቀበሉ አካላት ላይም ህግ የማስከበር ስራዎች ቀጥለው እንደሚከናወኑ መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከመጠናቀቁ በፊት ባሉት ጊዜያት ውስጥ የሚሰሩ ተግባራትን የማጠናቀቅ ስራ እንደሚሰራ መግለጹ ይታወሳል።