ፀጋዎቻችንን ወደ ተጨባጭ ኃብት በመቀየር የተሻለች ኢትዮጵያን የመገንባት ሥራችንን አጠናክረን እንቀጥላለን – ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ

የጨበራ ዝሆን ዳና ሎጅ

ታኅሣሥ 13/2016 (አዲስ ዋልታ) ፀጋዎቻችንን ወደ ተጨባጭ ኃብት በመቀየር የተሻለች ኢትዮጵያን የመገንባት ሥራችንን አጠናክረን እንቀጥላለን ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የገበታ ለሀገር ኮይሻ ፕሮጀክት አካል የሆነውን የጨበራ ዝሆን ዳና ሎጅ መርቀው በከፈቱበት ወቅት ኢትዮጵያ በብዙ ፀጋዎች የታደለች አገር ናት፤ ለዚህም የኮንታ ዞን የታደለው የተፈጥሮ ፀጋ ሁነኛ ማሳያ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ሦስት ነገሮችን አጥብቀን መሻትና ማስተዋል ይገባናል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ እነዚህም የማየት፣ የመሥራት እና ጠብቆ የማስቀጠል ብልጽግናዎች መሆናቸውን ገልፀዋል።

የማየት ብልጽግና የሚባለው ፊት ለፊት የሚታየውን ነገር በአግባቡ መመልከትና የተሻለ ዕድል መኖሩን ማስተዋል መሆኑን ተናግረው የማየት ብልጽግናን ያልታደለ ሰው በአጠገቡ ያለው ኃብት ዕዳ ሊሆንበት ይችላል ብለዋል።

የተሰጡንን ፀጋዎች ማየት ካልቻልን ሌሎች ማየት የሚችሉ ሊወስዱብን እንደሚችሉም ነው የጠቆሙት።

ብዙዎች የማየት ብልጽግና ባለመታደላቸው ኃብት ላይ ተቀምጠው ኃብታቸውን ሌሎች ሲወስዱባቸው እንደሚስተዋል አንስተው ፀጋዎቻችንን በሚገባ ማየት ያስፈልገናል ብለዋል።

የማየት ብልጽግና ብቻውን ውጤት እንደማያመጣ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የመሥራት ብልጽግና መከተል እንዳለበትና ኃብት በሥራ ካልተገለጠ ዋጋ ስለማይኖረው ከማየት በኋላ ተግቶ መሥራት ወሳኝ መሆኑን ገልፀዋል። ለዚህ ደግሞ እጅን ከሌብነት፣ ልብን ከክፋት ማፅዳት እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል።

ከማየትና ከመሥራት ብልጽግና በኋላ ደግሞ የመጠበቅና የማስቀጠል ብልጽግና አስፈላጊ መሆኑን አንስተዋል።

በአንድ በኩል ታሪክን መጠበቅና ማስቀጠል እንደሚገባ ጠቅሰው በሌላ በኩል ጎብኚዎች ከሚጠሏቸው ነገሮች ራስን መጠበቅ እንደሚያስፈልግ ገልፀዋል።

ጎብኚዎች የኢትዮጵያን ሕዝብ ደግነት፣ እንግዳ ተቀባይነትና ተባባሪነት እንደሚወዱ ገልጸው በሰላም እጦት ምክንያት ኢትዮጵያን በብቃት ለማየት እንደሚቸገሩ ጠቁመዋል።

በመሆኑም የማያግባቡን ነገሮች ቢኖሩም እኛንና ሀገራችንን ለማየት ለሚመጡ ጎብኚዎች ተገቢውን ጥበቃ ማድረግ ይገባል ብለዋል። ይህ ደግሞ የፖሊስ ሥራ ብቻ ሳይሆን የሁሉም ዜጋ ኃላፊነት መሆኑን አመልክተዋል።

ጎብኚዎች ሌላው የሚጠሉት ነገር ሌብነትና ልመና መሆኑን በመጥቀስ ሀገርን በመጥፎ ከሚያስጠሩ ነገሮች መቆጠብ እንደሚያስፈልግ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

የማየት፣ የመሥራትና ጠብቆ የማስቀጠል ብልጽግና ላይ በማተኮር ፀጋዎቻችንን ወደ ተጨባጭ ኃብት በመቀየር የተሻለች ኢትዮጵያን የመገንባት ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም አረጋግጠዋል።