የተከበራችሁ የሀገራችን ሕዝቦች፣
ኢትዮጵያ በረጅም ዘመን የሀገረ መንግሥትነት ታሪኳ፣ የፖለቲካ ልዩነቶችን፣ አለመግባባቶችን እና ግጭቶችን በሰላማዊ መንገድ፣ በንግግር፣ በውይይት እና በሕጋዊ አግባብ የመፍታት ልምምድ የላትም። እንደ አለመታደል ሆኖ ፖለቲካችን የዜሮ ድምር ፖለቲካ ነው። በሀገራችን የተለመደው በጉልበት አሸንፎ ሥልጣን የያዘ ኃይል፣ በጉልበት ተሸንፎ ሥልጣን እስኪለቅ ድረስ ሁሉንም ጠቅልሎ የሚቆጣጠርበት እና የፈቀደውን የሚያደርግበት የፖለቲካ ባህል ነው።
የለውጡ መንግሥት ወደ ሥልጣን የመጣው በጉልበት አይደለም። ይሄም አዲስ የፖለቲካ ባህል ነው። ይሄን አዲስ የፖለቲካ ምእራፍ የሚያጸና ሌላ ሰላማዊ የፖለቲካ ባህል ደግሞ በዴሞክራሲያዊ ምርጫ የሕዝብ ይሁንታ አግኝቶ መንግሥት በመመሥረት አሳይቷል። ከዚህም በመሻገር ልዩ ልዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮችና አባላትን በመንግሥት ኃላፊነት በመመደብ፣ ኢትዮጵያ የጋራ ቤት መሆንዋን አስመስክሯል።
ሰላማዊ የፖለቲካ ሽግግር ብቻውን ግብ አይደለም። ሌሎች ግቦችን ለማሳካት መሣሪያ እንጂ። የኢትዮጵያ ችግር የአሁኑን አካሄድ በማስተካከል ብቻ አይፈታም። በታሪክ ውስጥ የወረስናቸውን ስብራቶች መጠገንም የግድ ይለናል። እነዚህን የታሪክ ስብራቶች ለመጠገን ሦስት ዓይነት መፍትሔዎች ተቀምጠዋል። ነባሩን ፖለቲካዊ ችግር በሀገራዊ ምክክር መፍታት፤ የቅርብ ዘመናችንን የፖለቲካ ችግር ደግሞ በሽግግር ፍትሕ እና በተሐድሶ ማረም።
በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ አንድ መንግሥት በምርጫ አሸንፎ ሥልጣን ቢይዝም እንኳን ብቻውን ሊወስናቸው የማይገቡ፣ ሀገራዊ እና አካታች ምክክር የሚፈልጉ ጉዳዮች አሉ። ይሄ ድምጽ መሰማት ከጀመረ ግማሽ ምእተ ዓመት እየዘለቀው ነው። የለውጡ መንግሥት እስከመጣበት እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ግን ሰሚ አላገኘም ነበር። የለውጡ መንግሥት ሐሳቡን መቀበል ብቻ ሳይሆን ይሄንን የሚያሣልጥ ገለልተኛ ተቋምም አቋቁሟል።
በዚህ ተቋም ውስጥ በኃላፊነት የተሰየሙት ክፍተኛ ልምድ እና ብቃት ያላቸው ገለልተኛ ኮሚሽነሮች ናቸው። እነዚህ ኮሚሽነሮች አካታች ሀገራዊ ምክክሩን የማከናወን ሰፊ ሥልጣን በሕግ ተሰጥቷቸዋል። በዚሁ መሠረት ባለ ድርሻ አካላትን በማማከር ሂደቱ ምን መምሰል አለበት የሚለውን ዝርዝር አካሄድ እና አሠራሩን ነድፈዋል። በአሁኑ ወቅት የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ በነደፈው አካሄድ መሠረት በ10 ክልሎች እና በሁለት የከተማ አስተዳደሮች ከየወረዳው በምክክሩ ሂደት የሚሳተፉ ተሳታፊዎችን የመለየት ሥራ አጠናቋል። በእያንዳንዱ ክልል እጅግ ጥብቅ እና አድካሚ የሆነ ሥራ ተከናውኗል። ማኅበረሰቡን ከታችኛው የአስተዳደር መዋቅር ጀምሮ አሳትፏል። በዚህም በምክክሩ አካሄድ የሚሳተፉ ዜጎች ተለይተዋል። ከ679 ወረዳዎች፣ እስካሁን 12,294 ተሳታፊዎች ተለይተዋል።
ይሄ አካሄድ የጉዳዩ ባለቤት የሆነውን ሕዝብ ማዕከል ያደረገ ነው። አጀንዳዎች እና የመፍትሔ ሐሳቦች ከላይ ወደ ታች ብቻ ሳይሆን ከማኅበረሰቡም ፈልቀው፣ በውይይት ዳብረው ወደ መሐል የሚመጡበት አካሄድ ነው። በጥቂት ሳምንታት ውስጥ ኮሚሽኑ በክልል ደረጃ የሚደረጉ የምክክር መድረኮችን ማካሄድ እንደሚጀምር ይጠበቃል። እንዲሁም የተሳታፊ ልየታ ባልተደረገባቸው ሁለት ክልሎች ላይ የተሳታፊዎች ልየታ በቅርቡ ይጠናቀቃል። በጉጉት የሚጠበቀው አካታች ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ በአጭር ጊዜ ውስጥ እንደሚካሄድ ተስፋ ይደረጋል።
ይሄንን በትውልድ መካከል አንዴ የሚገኝ ዕድል ሳናባክን፤ እያቃናንና እየደገፍን፣ ለኢትዮጵያ ነባር ችግሮች መፍትሔ አዋላጅ እንዲሆን፣ ሁላችንም የድርሻችንን ልንወጣ ይገባናል። ዕድሎችን በሰበብ አስባቡ እያባከንን፣ ራሳችንን በችግር አዙሪት የማክረም አካሄድ ማብቃት አለበት።
ሁለተኛው የሽግግር ፍትሕ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ የታሪክ አጋጣሚዎች በደል፣ ግፍ እና መሠረታዊ የመብት ጥሰቶች ተከሥተዋል። ይህ በሌሎች ሀገራት ታሪክም የሚታይ ክሥተት ነው። እስከዛሬ ባለው አካሄዳችን በጉልበት አሸናፊ ሆኖ ሥልጣን የያዘው አካል፣ ሌሎችን በዳይ እና አጥፊ አድርጎ ይኮንናል፤ ይቀጣል። ይህ አካሄድ ግን ፍትሕን አያሰፍንም። እልህን፣ ቁጭትን እና የበቀል ጥማትን ያገነግናል እንጂ። የቁርሾ እና የቂም በቀል አዙሪት፣ የተበዳይነት እና የብሶት ትርክት በሀገራችን ዋነኛው የፖለቲካ ማጠንጠኛ የሆነበት አንዱ ምክንያትም ይሄው ነው። ይሄንን የበዳይ ተበዳይ አዙሪት ለመስበር የሽግግር ፍትሕ አንዱ ተመራጭ ስልት ነው። ስለዚህም የሽግግር ፍትሕ ሂደት የሚመራበት የፖሊሲ ማሕቀፍ ጸድቋል።
የፖሊሲው ዝግጅት የሚመለከታቸውን አካላት ያሳተፈ፣ ዓለም አቀፍ ልምድን መሠረት ያደረገ ነው። በቅድመ ፖሊሲ ማርቀቅ ሂደቱ ብቻ 60 የክልል እና 20 ሀገራዊ የግብአት ማሰባሰቢያ መድረኮች ተካሂደውበታል። የፖሊሲው ዓላማ የሽግግር ፍትሕ ሂደት የሚመራበት እና የሚተገበርበትን ሥርዓት በመዘርጋት ዘላቂ ሰላምን፣ ዕርቅን፣ የሕግ የበላይነትን፣ ፍትሕን እና ዴሞክራሲን ማረጋገጥ ነው። ይሄንን ዓላማ ለማሳካት እንደ አግባብነቱ የወንጀል ምርመራ እና ክስ፣ እውነት ማፈላለግ፣ ዕርቅ፣ በቅድመ ሁኔታ ላይ የተመሠረተ ምሕረት፣ ማካካሻ እና ተቋማዊ ማሻሻያ እንደ ሽግግር ፍትሕ ስልቶች በሀገራችን ተግባራዊ ይደረጋሉ።
እንደሚታወቀው በሀገራችን ከመንግሥት ውጭ የሚኖር የታጠቀን ኃይል ሕገ መንግሥታችን አይፈቅድም። የመንግሥትም አንዱ መብት በብቸኝነት ኃይልን መጠቀም ነው። ነገር ግን በሀገራችን በወረስነው የፖለቲካ ስብራት የተነሣ የታጠቁ ኃይሎች ተፈጥረዋል። ሰላማችንን የጸና ለማድረግ፣ እነዚህ የታጠቁ ኃይሎች ትጥቅ ፈትተው፣ የተሐድሶ ሂደት ውስጥ መቀላቀል አለባቸው። የፖለቲካ ጥያቄዎቻቸውንም በሀገራዊ ምክክር ሂደት በመሳተፍ መፍታት ይችላሉ። ለዚህ የሚሆን የተሐድሶ ኮሚሽን ተቋቁሟል። ዓላማውም መሣሪያ ማስፈታት፣ የትጥቅ ቡድኖችን ሰላማዊ ማድረግና ከማኅበረሰቡ ጋር መቀላቀል ናቸው። ይሄንን የተሐድሶ ሥራ በማሳካት ፖለቲካችን ከግንባር ወደ ጠረጴዛ፣ ከጫካ ወደ አዳራሽ እንዲመለስ ማድረግ አለብን። እነዚህን ስልቶች በሚገባ ተግባራዊ በማድረግ፣ ከበዳይ ተበዳይ አዙሪት ልንወጣ ያስፈልጋል። በምሕረት፣ በይቅርታ፣ በካሣና፣ በፍትሕ ታክመን ወደፊት መጓዝ መቻል አለብን። ለዚህ ስኬትም ኢትዮጵያውያን ሁሉ በንቃትና በብቃት ልንሳተፍ ይገባናል። መንግሥትም የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ አተገባበርን ከሀገራዊ ምክክር ሂደቱ ጋር የተናበበ እና የሚመጋገብ እንዲሆን በማድረግ ኃላፊነቱን ይወጣል።
ነባር ሀገራዊ ችግሮቻችንን በሀገራዊ ምክከር እና በሽግግር ፍትሕ እያረምን የገጠሙን የግጭትና የጦርነት ፈተናዎች ለመሻገር ደግሞ ሰላማዊ የፖለቲካ አካሄዶችን ተመራጭ ማድረግ አለብን። ለሁለት ዓመታት የዘለቀውን የሰሜኑን ጦርነት በሰላም ስምምነት ለመፍታት የተፈለገውም ለዚህ ዓላማ ነው። በኢትዮጵያ ታሪክ በተለያዩ ወቅቶች የእርስ በርስ ግጭቶች እና ጦርነቶች በተደጋጋሚ ተከሥተዋል። በእነዚህ ጦርነቶች እንደ ሀገር ከባድ ኪሣራ ደርሶብናል። የዚህም ምክንያቱ ግጭቶችን በንግግር እና በስምምነት የመፍታት የፖለቲካ ልምምድ ብዙም ስለሌለን ነው። የለመድነው በጠላታችን መቃብር ላይ ሐውልት መገንባት ነው።
የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ይሄንን ነባር ልማድ ቀይሮታል። ጦርነትን በፖለቲካዊ መፍትሔ የመቋጨት ባህል አምጥቷል። ይሄ የሰላም ስምምነት ለትውልድ የአሸናፊ ተሸናፊ ትርክትን ከቂም ጋር ላለማውረስ የተደረገ በሳልና ቆራጥ ውሳኔ ነው። ይሄንን አማራጭ ተከትለን፣ ደም መፋሰስ እና ግጭትን ማቆም ችለናል። በአማራ፣ በአፋርና በትግራይ ክልሎች የመልሶ ግንባታ እና የመልሶ ማቋቋም ሥራዎች ተጀምረዋል። ሰብአዊ ድጋፍም ያለመሰናከል ወደ ትግራይ መድረስ የሚችልበትን ዐውድ ፈጥረናል። የሰላም ስምምነቱ በተፈረመ ማግሥት መንግሥት በሰላም ስምምነቱ ከገባው ግዴታ ያለፈ፣ መተማመን ለመፍጠር እና ሰላምን ለማጽናት አስፈላጊ ናቸው ያላቸውን ርምጃዎች በተከታታይ ወስዷል።
በሰላም ስምምነቱ እስካሁን የተገኘው ውጤት እና እፎይታ እንደተጠበቀ ሆኖ ቀሪ ሥራዎችም አሉ። በተለይ በስምምነቱ መሠረት የሕወሐት ታጣቂዎች ትጥቅ መፍታት አለባቸው። የማንነት እና የአስተዳደር ወሰን ጥያቄ ያለባቸውን አካባቢዎች ጉዳይ እልባት ለመስጠት እንዲቻል የተቀመጠው አቅጣጫ ተግባራዊ መደረግ አለበት። በጦርነቱ የተፈናቀሉትን ለመመለስና ለማቋቋም የተጀመረው ሥራ እልባት ማግኘት አለበት። ካለፈ ስሕተተ አለመማር የመጀመሪያውን ስሕተት ከመሥራት የባሰ ነው። ካለፈው ስሕተታቸው ሳይማሩ ዛሬም ተመሳሳይ ችግር ለመፍጠር የሚከጅሉትን ሁላችንም ተባብረን አደብ ማስገዛት ይኖርብናል። ከትዕግሥት በኋላ የሚከሠት ሕግ የማስከበር ሥራ የሚኖረውን አስከፊ ውጤት ከቅርቡ ታሪካችን ልንማር ይገባልና።
መንግሥት የተቋረጡ መሠረት ልማቶችን እና አገልግሎቶችን ለመጠገን እና መልሶ ለማስጀመር ወገቡን አሥሮ እየሠራ ነው። የፋይናንስ እና የኢኮኖሚ እንቅስቃሴን በትግራይ ክልል ለማሣለጥ እጅግ ከፍተኛ ወጪ አውጥቷል። የሰላም የትርፍ ድርሻው ታላቅ በመሆኑ መንግሥት ከሚጠበቅበትም አልፎ ቁስልን ለመሻር የሚያስችል ሥራ እየሠራ ነው። ይሄ ግን መንግሥታዊ ኃላፊነት እንጂ ፍርሃት ተደርጎ መወሰድ የለበትም።
በፕሪቶሪያ ስምምነት እንደተገለጸው፣ በሕገ መንግሥታችንም እንደተደነገገው፣ እንደ ሀገር የሚኖረን አንድ የመከላከያ ሠራዊት ብቻ ነው። ክልሎች በክልል ደረጃ ሕግ ለማስከበር ከሚያስፈልጋቸው ፖሊስ እና ሚሊሺያ ያለፈ የታጠቀ እና የተደራጀ ሠራዊት ሊኖራቸው አይችልም፤ አይገባምም። በዚህ መሠረት ትጥቅ መፍታት እና ተያያዥ ሂደቶች በተሐድሶ ኮሚሽኑ ዕቅድ መሠረት በፍጥነት ሊተገበሩ ይገባል።
ወንድሞቻችን/እኅቶቻችን በተለይም ወጣቶች በተለያዩ ምክንያቶች ተገፋፍተው በጽንፈኞች እና በግጭት ጠማቂዎች ወደ ጦር ዐውድማ የሚማገዱበት አጋጣሚ አለ። መንግሥት ይሄንን ሁኔታ ከአንድ አቅጣጫ ብቻ አያየውም። እንቅስቃሴያቸው ሕገ ወጥ ስለሆነ ብቻ ጉዳዩን በጉልበት ብቻ ይፈታ ማለት እንደሌለበት ይገነዘባል።
ስለዚህ ከጥፋት መንገድ ለመመለስ እና ማኅበረሰቡን ተቀላቅለው ሰላማዊ ሕይወት ለመኖር ፍላጎት ያላቸውን ታጣቂዎች ሁሉ፣ በተዘረጋ እጅ ለመቀበል መንግሥት ፈቃደኛ ነው። ይሄንን ፈቃደኝነቱን እና ፍላጎቱን በተግባር በተለያዩ ክልሎች አሳይቷል። በቤነሻንጉል ጉሙዝ፣ በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች በዐሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ታጣቂዎች እጃቸውን ሰጥተዋል። እነዚህም የተሐድሶ ሥልጠና ወስደው፣ ከማኅበረሰቡ ጋር እንዲቀላቀሉ ተደርጓል። ይሄንንም በተሐድሶ ኮሚሽን በኩል ከክልሎች ጋር በመቀናጀት አጠናክረን እንቀጥላለን። ጥረቱን የሀገር ሽማግሌዎች እና የሃይማኖት አባቶች እንዲደግፉ በዚሁ አጋጣሚ ጥሪ እናደርጋለን።
እነዚህን ዘላቂ መፍትሔ አምጪ ሥራዎች በአንድ በኩል እያከናወንን የሕዝቡን ሰላምና ደኅንነት የሚያስከብሩ አሁናዊ ተግባራትንም ማከናወናችንን እንቀጥላለን። ጽንፈኛ የፖለቲካ አመለካከቶች እንዲሁም የተደራጁ የወንጀል እና የዘረፋ ፍላጎቶች በአንዳንድ አካባቢዎች እየታዩ ናቸው። እነዚህን በገጠርም ሆነ በከተማ የሕዝብን ሰላም የሚያውኩ እንቅስቃሴዎች ለመቆጣጠር መንግሥት ሰፊ ሥራ እየሠራ ነው።
የዚህ ሥራ አንዱ አካል፣ የሕግ አስከባሪ ተቋማትን እያሻሻሉ ፤ ቅንጅታቸውን እና ከሕዝብ ጋር ያላቸውን ትሥሥር እያጠናከሩ እንዲሄዱ ማድረግ ነው። በገጠር ቀበሌዎች እና መንደሮች፣ የየአካባቢው ነዋሪ በአግባቡ ሠልጥኖ አካባቢያዊ ሰላሙን ለማስከበር እንዲችል ይደረጋል። በዚህ ረገድ በአንዳንድ ክልሎች በጎ ጅምር አለ። እንደ ኢትዮጵያ ላለ እጅግ ሰፊ እና ብዙ ሕዝብ ላለበት ሀገር፣ የአካባቢ ሚሊሽያ እና ሌሎች አጋዥ ሰላም አስከባሪ አደረጃጀቶች አካባቢያዊ ሰላም እና ጸጥታን ለማስከበር ትልቅ ሚና አላቸው።
ከዚያ በተጨማሪ፣ የክልል ፖሊስ ኃይሎችን መልሶ በማደራጀት እና በሁለንተናዊ መልኩ በማጠናከር፣ ሕገ መንግሥታዊ ተልዕኳችውን በአግባቡ እንዲወጡ እየተደረገ ነው። በየአካባቢው ካሉት ሚሊሺያዎች እና የክልል ፖሊሶች ጋር በመቀናጀት፣ የፌደራል ፖሊስ የሀገር ውስጥ ሰላም እና ሕግ የማስከበር ኃላፊነቱን እንዲወጣ ቀጣይነት ያለው ተቋም ግንባታ እና ማሻሻያ እየተካሄደ ነው። ከእነዚህ ሕግ አስከባሪ ተቋማት ያለፈ ሥጋት ካጋጠመ፣ የሀገር መከላከያ ሠራዊት ሰላም የማስጠበቅ እና ሕግ የማስከበር ተግባሩን እየተወጣ ይገኛል።
ይሄንን ዓይነት የጸጥታ አካላትና የሕዝብ ቅንጅት በመኖሩ፣ በአማራ ክልል የክልሉን መንግሥት አፍርሶ በኃይል ሥልጣን ለመያዝ ያሰበው ኃይል ፍላጎቱን ለማሳካት እንዳይችል ተደርጓል። በተሠራው የሕግ ማስከበር ሥራ፣ የክልሉን መንግሥት እና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ለመታደግ ተችሏል። በኦሮሚያ ክልልም በአንዳንድ የክልሉ ዞኖች የነበረው የታጣቂ ኃይሎች ሰፊ እንቅስቃሴ እና አንዳንድ ወረዳዎችን የመቆጣጠር አዝማሚያ ተቀልብሷል። በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልልም የጸጥታና የደኅንነት ሁኔታው በእጅጉ ተሻሽሏል። በአዲስ አበባ እና በሌሎችም የሀገሪቱ ትላልቅ ከተማዎች የተለያዩ የሽብር ጥቃቶችን ለመፈጸም አቅደው የሚንቀሳቀሱ ኃይሎችን ዕቅድ ለማክሸፍም ተችሏል።
የተሠራው ሥራ ወሳኝ ቢሆንም በቂ ግን አይደለም። ፖለቲካ ቅብ የሆኑ የተደራጁ የዝርፊያ እና የወንጀል ቡድኖችን በሚገባ መቆጣጠር ይገባናል። ይሄንን ለማድረግም ጠንካራ እና ውጤታማ ሕግ አስከባሪ እና የጸጥታ መዋቅር እንዲኖረን የተጀመረው ሥራ ይቀጥላል። በዚህ ረገድ የሕዝብ ተሳትፎ እና እገዛ ወሳኝ ነው። እየዘረፈ፣ እየነጠቀ እና እያገተ ያለን ቡድን በተለያየ ሰበብ መሸከም እና ማባባል ማብቃት አለበት። በድኻ ገንዘብ የተሠሩ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተቋማትን የሚያወድም ቡድን የማንንም ፍላጎት አያስከብርም። ሕዝቡ ከሕግ አስከባሪ አካላት ጋር በመተባበር የሕግ የበላይነትን ማስከበር ይገባዋል። በየአካባቢው የሚገኙ የፖለቲካ እና የአስተዳደር መዋቅሮችም፣ ሌላ አካል መጠበቅ ሳይሆን፣ ሕግን ማስከበር ቀዳሚ ኃላፊነታቸው እንደሆነ ተገንዝበው ሊንቀሳቀሱ ይገባል።
በአንድ በኩል ሕግ የማስከበርና ሰላምና ደኅንነትን የማጽናት ሥራ እያከናወንን፤ በሌላ በኩል ደግሞ የተፈናቀሉ ሰዎችን የመመለስ ተግባር መከናወን አለበት። ሰላምና ጸጥታ ሕዝብ ሲረጋጋ የሚፈጠሩ ሥርዓቶች በመሆናቸው። በሀገራችን በተለያዩ ምክንያቶች፣ ሰዎች ከመኖሪያ አካባቢያቸው ተፈናቅለዋል። እነዚህ ዜጎች ከመጠለያ ካምፖች ወጥተው ወደቀያቸው መመለስ ይኖርባቸዋል። በዘላቂነት ተረጋግተው ወደ መደበኛ ኑሮ መግባት አለባቸው። ይሄንን እውን ለማድረግ መንግሥት ሲተጋ ቆይቷል፣ አሁንም ሰፊ ሥራ እየሠራ ይገኛል። ለምሳሌ በሶማሌ እና ኦሮሚያ አዋሳኝ አካባቢዎች፣ እንዲሁም በጌዴኦ አካባቢ ተፈናቅለው የነበሩ ዜጎች ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ እና ዘላቂ መኖሪያ እንዲያገኙ ለማድረግ ተችሏል።
በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ባጋጠመው ግጭት፤ እንዲሁም በኦሮሚያ እና በአማራ ክልሎች ባጋጠሙ የጸጥታ ችግሮች የተነሣ የተፈናቀሉ ዜጎች አሉ። እነዚህ ተፈናቃዮች ወደ ቤታቸው እንዲመለሱ እየሠራን ነው። የአማራ እና የኦሮሚያ ክልል አመራሮች በጋራ ሠርተው ብዙዎችን ከመጠለያ ጣቢያ ወደ ቤታቸው እንዲመለሱ አድርገዋል። በዚህ ሂደት በማኅበረሰቡ ዘንድ ወትሮም የነበረውን መተሳሰብ እና ጥብቅ ትሥሥር ለማየት ተችሏል። የተፈናቀሉ ጎረቤቶቻቸው እንዲመለሱ በየአካባቢው ከፍተኛ ፍላጎት አለ። ለሚመለሱት ተፈናቃዮች የየአካባቢው ማኅበረሰብ የሚያደርገው አቀባበል ልብ የሚጠግን ነው። በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ለምሳሌ በራያ እና አላማጣ አካባቢ ከተፈናቀሉ ዜጎች መንግሥትን ሳይጠብቁ በማኅበረሰባዊ መተሳሰብ ብቻ በርካታዎች ወደ ቤታቸው ገብተዋል።
በዚህ ሂደት የተፈናቃዮችን ጉዳይ እንደ ፖለቲካ አጀንዳ አድርገው ሊጠቀሙ የሚፈልጉ አካላት መኖራቸው ታይቷል። ተፈናቃዮች ከተመለሱ የልመናና፣ የተቃውሞ አጀንዳችን ይከስራል ብለው ይፈራሉ። እነዚህ ኃይሎች ተፈናቃዮቹ ወደ ቤታቸው እንዳይመለሱ ፕሮፖጋንዳ እና ማስፈራሪያ ይደረድራሉ። አንዳንዴም በኃይል ጭምር የተፈናቃዮችን መመለስ ለማሰናከል ይቃጣቸዋል። መንግሥት ካለበት የሞራል እና የሕግ ኃላፊነት የተነሣ የተፈናቀሉ ዜጎች ወደ ቤታቸውና ወደ መኖሪያቸው እንዲመለሱ ማድረጉን ይቀጥላል። ከክልሎች ጋር የተጀመረው ሥራም ይጠናከራል።
ሰላምና ጸጥታን ለማደፍረስ፣ የተፈናቀሉ ወገኖች እንዳይመለሱ ለማድረግና የልማት ተግባራትን ለማሰናከል አንዱ የመዋጊያ መሣሪያ የተዛባ፣ የተሳሳተና የተመረዘ መረጃን ማሠራጨት ነው። እንደሚታወቀው የመገናኛ ቴክኖሎጂ ዕድገት ዕድልም፣ አደጋም ይዞ መጥቷል። በዚህ ዘመነ መረብ ሽኩቻ እና ፉክክር ይበዛል። ነባር ተቋማት እና ሥርዓቶች በእጅጉ ፈተና ላይ ይወድቃሉ። በዚህ ዐውድ ውስጥ ሀገራት ብሔራዊ ጥቅማቸውን ለማስከበር ያለ ይሉኝታ እና ያለ ብዙ ልጓም የቻሉትን ሁሉ ያደርጋሉ።
በዚህ ወቅት ሁኔታውን በአግባቡ በመረዳት፣ ይሄንን ማዕበል እና ወጀብ እንዴት ማለፍ አለብን የሚለውን በጥንቃቄ ተልመን ካልተንቀሳቀስን አደጋው ከባድ ነው። በዚህ ረገድ ውጤታማ ለመሆን የውስጥ አንድነት እጅግ ወሳኝ ነው። እንደ ኢትዮጵያ ያለ ትልቅ ሀገር የውስጥ አንድነት ካለው ነጥሮ ይወጣል። እንደ ሀገር እና እንደ ሕዝብ ለአንድ ዓላማ በጋራ ከተሰለፍን ወቅቱ ሀገራችንን ከፍ ለማድረግ የራሱን በጎ አጋጣሚዎች ይዞ ይመጣል። ከተከፋፈልን ደግሞ የሀገር ህልውና አደጋ ላይ ይወድቃል። ስለዚህም የሚመጡ መረጃዎችን መምረጥ፣ መመዘንና ማንጠር አስፈላጊ ነው። በምድር ያሸነፍናቸው ጠላቶቻችን በአየር እንዲመጡ መፍቀድ የለብንም።
እነዚህን ሁሉ የምናከናውነው መጀመሪያ ዘላቂ ሰላም፤ በዘላቂ ሰላም በኩልም ዘላቂ ብልጽግናን ለማረጋገጥ ነው። እንደ መንግሥት ግባችን በአቋራጭ መንገድ፣ ከላይ ከላይ በሆነ እድሳት የሚመጣ ጊዜያዊ ጸጥታ አይደለም። ዘላቂ ሰላም ነው። ዘላቂ ሰላም የጦርነት አለመኖር ብቻ አይደለም። በመርሕ እና በሥርዓት ላይ የተመሠረተ፣ በቀላሉ የማይናወጥ ሰላም ነው። ግጭትን፣ እና አለመግባባትን በሰላማዊ እና በሕጋዊ መንገድ ለመፍታት የሚያስችል ዐቅም እና ሥርዓት መኖር ነው። በመሠረታዊ ጉዳዮች ላይ በመግባባት፣ ያለፈን ቁርሾ እና የታሪክ ጠባሳን አልፎ ወደፊት ለመሄድ መቻል ነው።
ይሄንን ዘላቂ ሰላምና ዘላቂ ብልጽግና ለማምጣት አዲስ የፖለቲካ ባህል የግድ ነው። ሁሉን አካታች ሀገራዊ ምክክር፣ የሽግግር ፍትሕ እና የተሐድሶ ተግባራት የዚህ ማከናወኛ ዋነኞቹ መሣሪያዎች ናቸው። ማንም እንደሚያውቀው አካታች የሆነ መንግሥታዊ እና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመገንባት ፈር ቀዳጅ እየሆንን ነው። ይህ ጥረት ውጤታማ እንዲሆን ግን የመንግሥት ተግባር ብቻውን በቂ አይሆንም። ገዢው ፓርቲ አዲስ የፖለቲካ ባህል ለማስተዋወቅ – አብረን እንሥራ፣ እንምከር፣ በጋራ ለሀገራችን ጉዳዮች መፍትሔ እንፈልግ እያለ ነው። አንዳንዶች ደግሞ በድሮ በሬ እያረሱ በጉልበት፣ በኃይልና በጠመንጃ መንግሥትን ጥለን ሥልጣን ጠቅልለን ካልወሰድን እያሉ ናቸው። እንደዚህ በተቃራኒ መንገዶች ተጉዘን የተጀመሩት ጥረቶቻችን ሊሳኩ አይችሉም። የ18ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ባህልን ይዞ በ22ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መሄድ ርግማን እንጂ ለውጥ አያመጣም።
ጦርነት ሁላችንንም ያከስራል። ሰላም ሁላችንንም አትራፊ ያደርጋል። እኛ ከአባቶቻችን ስለጦርነት እየሰማን አደግን፤ ይበቃናል። በእኛ ትውልድ እንኳን ሁለትና ሦስት ከባድ ጦርነቶች አለፉ። ለቀጣይ ትውልድ ግን ብልጽግናን እንጂ ቁስልን ማውረስ የለብንም። የኢትዮጵያን ዘመናዊ የፖለቲካ ቅኝት ለሃምሳ ዓመት የበየነው የ1966ቱ አብዮት ከተከሠተ ግማሽ ምእተ ዓመት ሆኖታል። አዙሪቱ ያልለቀቃቸው ግን አሁንም አሉ። ካለፈው ተምረን፣ የራሳችንን እና የዘመናችንን ዐውድ ተገንዝበን፣ በራሳችን ቅኝት እና አጀንዳ ወደፊት ልንራመድ ይገባል። የዚህ ትውልድ የሃምሳ ዓመት አጀንዳ ዘላቂ ሰላም እና ሁለንተናዊ ብልጽግና ነውና።
የብሔራዊ ደህንነት ምክር ቤት
ሚያዚያ 16፣ 2016 ዓ.ም
አዲስ አበባ