ኢትዮ ቴሌኮም በ29 ከተሞች ብሔራዊ የዲጂታል መታወቂያ ምዝገባ አስጀመረ


ሚያዝያ 16/2016 (አዲስ ዋልታ) ኢትዮ ቴሌኮም አዲስ አበባን ጨምሮ በ29 ከተሞች ብሔራዊ የዲጂታል መታወቂያ (ፋይዳ) ምዝገባ በይፋ አስጀመረ።

ይህም ሁሉም ዜጎች ብሔራዊ የዲጂታል መታወቂያ ባለቤት እንዲሆኑ ለማድረግ ያለመ ነው ተብሏል።

የዲጂታል መታወቂያን በሀገር አቀፍ ደረጃ በ2018 ዓ.ም 90 ሚሊዮን ለሚሆኑ ዜጎች ለማዳረስ መታቀዱ የተገለፀ ሲሆን ከዚህ ውስጥ ኢትዮ ቴሌኮም 1 ሚሊዮን ዜጎችን በመመዝገብ ለ32 ሚሊዮን ዜጎች ተደራሽ በማድረግ የሀገራዊ እቅዱን 36 በመቶ የሚያከናውን መሆኑ ተገልጿል::

የኢትዮጵያ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩ በማስጀመሪያ ሥነ ሥርዓት ላይ በሀገር አቀፍ ደረጃ የዲጂታል ዘርፍን ለማስፋፋት በርካታ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን አስታውሰው የዲጂታል መታወቂያም የዚሁ አንድ አካል ነው ብለዋል::

ብሔራዊ የዲጂታል መታወቂያ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች እንዳሉት ያነሱት ዋና ሥራ አስፈፃሚዋ ከዚህ ውስጥም አካታች የዲጂታል ኢኮኖሚን ለማስፋፋት፣ የግብይት ሥርዓትን ለማሳለጥና ለዲጂታል ኢኮኖሚው እድገት ከፍተኛ አስተዋጽዖ እንደሚኖረው ተናግረዋል።

በሌላ በኩል የዜጎችን ሰላምና ደህንነት ለመጠበቅ እንዲሁም ወንጀልን ለመከላከል ብሎም የአገልግሎት ሰጪ ተቋማትን ሥራ በማሳለጥ በግልጋሎት እና ተገልጋይ መካከል ያለውን ድልድይ ከማጥበብ ረገድ ፋይዳው ከፍ ያለ መሆኑንም ገልፀዋል::

በሔብሮን ዋልታው