በዋልታ ቲቪ ፓርቲዎች ከ75% በላይ የሚሆነውን ነጻ የአየር ሰዓት መጠቀማቸው ተገለጸ

ግንቦት 19/2013 (ዋልታ) – እስካሁን ፓርቲዎች በዋልታ ቴሌቪዥን በተደለደለላቸው ነጻ የአየር ሰዓት ከ75 በመቶ በላይ መጠቀማቸውን የዋልታ ሚዲያና ኮሙኒኬሽን ኮርፖሬት ምርጫ ዴስክ አስታወቀ፡፡

ለ6ኛው ጠቅላላ ምርጫ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለምረጡን ቅስቀሳ የሚጠቀሙበት ነፃ የአየር ሰዓት ከመጋቢት 30/2013 ዓ.ም እስከ ግንቦት 23/2013ዓ.ም ድረስ መደልደሉ የሚታወቅ ሲሆን በዚህም መሰረት በጣቢያው የተደለደለውን የአየር ሰዓት አጠቃቀም እስከ ግንቦት 19/2013 ዓ.ም ድረስ ያለውን ሪፖርት የዋልታ ሚዲያና ኮሙኒኬሽን ኮርፖሬት ምርጫ ዴስክ ይፋ አድርጓል፡፡

የመጠባበቂያ የተመደበውን የአየር ሰዓት ጊዜ ሳይጨምር በዋልታ ሚዲያ ለምርጫ ቅስቀሳ በአጠቃላይ በመደበኛነት የተመደበው የጊዜ መጠን 375 ደቂቃ ሲሆን እስከ ግንቦት 19/2013 ዓ.ም ድረስ ለምርጫ ቅስቀሳ ከተመደበው 300 ደቂቃ ፓርቲዎቹ ከ75 በመቶ በላይ መጠቀማቸው ተገልጿል፡፡

በዋልታ ሚዲያ የምርጫ ቅስቀሳ እንዲያደርጉ 11 ፓርቲዎች ነፃ የአየር ሰዓት የተፈቀደላቸው ሲሆን አንድ የግል ተወዳዳሪ (ዲያቆን ዳንኤል ክብረት) በመጠባበቂያ ሰዓት ቅስቀሳ እንዲያደርጉ ተፈቅዶላቸዋል፡፡

ይሁን እንጂ እስከ ግንቦት 19/2013 ድረስ የዋልታ ሚዲያ የምርጫ ቅስቀሳ ነፃ የአየር ሰአትን ሶስት የፖለቲካ ፓርቲዎች ማለትም የኢትዮጵያ ዴሞክራቲክ ህብረት፣ አብን፣ ህብር ኢትዮጵያ ወደ ጣቢያው ባለማምጣታቸው ምክንያት የአየር ሰዓቱን አልተጠቀሙበትም፡፡

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ(ኢዜማ) ከተሰጡት ነጻ የአየር ሰዓት አንድ ቀን ብቻ አለመጠቀሙን የገለጸው ምርጫ ዴስኩ ፓርቲዎች የተደለደለላቸውን ነፃ የአየር ሰዓት በአግባቡ እንዲጠቀሙ አሳስቧል፡፡

በተመሳሳይ የዋልታ ሚዲያና ኮሙኒኬሽን ኮርፖሬት ምርጫ ዴስክ 6ኛውን ጠቅላላ ምርጫ አስመልክቶ የተዘጋጁ የክርክር መድረኮችን እና የፖለቲካ ፓርቲዎች የምረጡኝ ቅስቀሳ ነፃ የአየር ሰዓት ሪፖርትም ይፋ አድርጓል፡፡

ዋልታ ሚዲያና ኮሙኒኬሽን ኮርፖሬት 6ኛውን ጠቅላላ ምርጫ አስመልክቶ በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች የክርክር መድረኮችን እያዘጋጀ መሆኑ ይታወቃል፡፡

በዚህም መሰረት በ11 ዙር 8 የፖለቲካ ፓርቲዎችን ለማከራከር እቅድ የተያዘ ሲሆን እስከ 19/09/13 ዓ.ም ድረስ በሰባት የክርክር ርእሰ ጉዳዮች ዙሪያ በስምንት ዙር አስር የፖለቲካ ፓርቲዎችን አከራክሯል፡፡

በመጀመሪያ ዙር በፌደራሊዝምና ብዝሀነት ዙሪያ ብልፅግና፣ ኢዜማ፣ አዲስ ትውልድ ፓርቲ እና ነፃነትና እኩልነት ፓርቲን ያከራከረ ሲሆን በተመሳሳይ ርእሰ ጉዳይ በሁለተኛ ዙር መኢአድ፣ ህብር ኢትዮጵያ፣ ኢህአፓ እና ብልፅግና ፓርቲን አከራክሯል፡፡

የህግ የበላይነት እና የዲሞክራሲ ስርአት ግንባታ ላይ ትኩረት በማድረግ ብልፅግና፣ ኢዜማ እንዲሁም ኢትዮጵያ ሶሻል ዲሞክራሲን በሶስተኛው ዙር ያከራከረ ሲሆን በግብርና፣ ገጠር ልማትና ምግብ ዋስትና ላይ ርእሰ ጉዳዩን በማድረግ በአራተኛ ዙር ለእናት ፓርቲ፣ ብልፅግና፣ አዲስ ትውልድ ፓርቲ እና መኢአድ ፓርቲ ተከራክረዋል፡፡

በተጨማሪም በህግ የበላይነትና በዲሞክራሲ ስርአት ግንባታን መነሻ አድርጎ የኢትዮጵያ ሶሻል ዲሞክራሲ፣ ኢዜማ እና ብልፅግናን ያከራከረው ኮርፖሬቱ በስድስተኛው ዙር ደግሞ ብልፅግና፣ ኢዜማ፣ አብን እንዲሁም ነፃነትና እኩልነት ፓርቲ በውጭ ጉዳይ እና ግንኙነት ፖሊሲ ዙሪያ እንዲከራከሩ ምቹ መድረክ ፈጥሯል፡፡

ህብር ኢትዮጵያ፣ አዲስ ትውልድ፣ ኢህአፓ፣ እና ብልፅግና ፓርቲን በኢንዱስትሪ ልማት እና መንግስት ሃላፊነት፤ ብልፅግና፣ እናት ፓርቲን እና መኢአድን በማህበራዊ ፖሊሲ (ትምህርትና ጤና) በሰባተኛና ስምንተኛ ዙር የክርክር መድረኩ አስተናግዷል፡፡