የውጭ ጫናዎችን ለመቋቋም ሁሉም ዜጋ ድጋፍ ማድረግ እንዳለበት ተጠቆመ

ግንቦት 19/2013 (ዋልታ) – ኢትዮጵያ አሁን የገጠሟትን ውስጣዊ ችግሮች እና የውጭ ጫናዎች መቋቋም እንድትችል እና ወደተሻለ ምዕራፍ እንድትሸጋገር ሁሉም ዜጋ በሚኖርበት ሀገር ሆኖ ድጋፍ ማድረግ እንዳለበት አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን አሳስበዋል፡፡

በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን የተመራ ልዑክ የኳታር ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሼክ መሃመድ ቢን አብዱራህማን አልታኒ እንዲሁም ከምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሱልጣን ቢን ሰዓድ አልሙሬይኪ ጋር በሁለትዮሽ እና ቀጠናዊ ጉዳዮች ዙሪያ ነው ውይይት ያደረጉት፡፡

አምባሳደር ሬድዋን በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታዎች፣ በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ፣ በኢትዮ-ኳታር ግንኙነት እና ከኳታር ባለስልጣናት ጋር ስለተደረገው ውይይት አብራርተዋል፡፡

በውጭ ሃገራት የሚኖሩ ዜጎች በተለያዩ ችግሮች ውስጥ የሚገኙ ቢሆንም፣ ኢትዮጵያ አሁን ከምትገኝበት ፈታኝ ሁኔታ በድል መውጣት እንድትችል መንግስት የሚያደርገውን ጥረት እንዲደግፉ እና ዓለም አቀፉን ጫና በመቋቋም ለሀገራቸው አለኝታነታቸውን እንዲያሳዩ መጠየቃቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ፅህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

በኳታር ዶሃ የሥራ ጉብኝት እያደረገ የሚገኘው የልዑክ ቡድኑ በኳታር ከሚገኙ የተለያዩ የዳያስፖራ አደረጃጀት አመራሮች ጋር ውይይት አድርጓል።