በየአከባቢ የሚገኙ የውሃ አማራጮችን በመጠቀም በበጋ የመስኖ ስንዴ ልማት የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ እንደሚቻል ተጠቆመ

ስንዴ ልማት

መጋቢት 28/2014 (ዋልታ) በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የግብርና ቢሮ ኃላፊ ማስረሻ በላቸው የተመራው ልዑክ በዳውሮ ዞን ኢሰራ ወረዳ በበጋ መስኖ የለማውን የስንዴ ምርት የማሰባሰብ ሂደት ጎብኝተዋል።

ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ በጉብኝታቸው ወቅት በየአከባቢ የሚገኙ የውሃ አማራጮችን በመጠቀም በበጋ የመስኖ ስንዴ ልማት የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ ይቻላል ብለዋል።

በበጋ መስኖ በአከባቢው የለማ የስንዴ ምርት በጣም ውጤታማ እንደሆነ ገልጸው የእርሻ ሥራው በበልግ ወቅትም ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባ አሳስበዋል።

በክልሉ ያለውን የምርጥ ዘር እጥረት ችግር ለመቅረፍ ምርጥ ዘርን በክልሉ አምርቶ የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ተግባራዊ እንቅስቃሴ እንደተጀመረም ገልፀዋል።

የዳውሮ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና መምሪያ ኃላፊ ታመነ ተስፋየ በበኩላቸው በዞኑ ለመጀመሪያ ጊዜ በ62 ሄክታር መሬት ተግባራዊ ከሆነው ከበጋ መስኖ ስንዴ አመርቂ ውጤት ማግኘት መቻሉን ተናግረዋል።

በሁሉም ዘርፍ ጠንክረን ከሰራን ድህነትን ማሸነፍ እንደሚቻልም መግለፃቸውን ከዞኑ መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ያገኘነው መረጃ አመላክቷል።

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW