በደብረ ብርሃን ከተማ ከኅብረተሰቡ ጋር የተደረጉ ወይይቶች ዘላቂ ሰላም ለመፍጠር መሰረት መጣላቸው ተገለጸ

ነሐሴ 15/2015 (አዲስ ዋልታ) ከኅብረተሰቡ ጋር የተደረጉ ወይይቶች ዘላቂ ሰላም ለመፍጠር መሰረት መጣላቸውን የደብረ ብርሃን ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባና የማዕከላዊ ሸዋ ኮማንድ ፖስት አባል በድሉ ውብእሸት ገለጹ።

የከተማዋን ወቅታዊ ሁኔታ በማስመልከት ማብራሪያ የሰጡት ኃላፊው የሸቀጦች የዋጋ ንረትን ለማቃለል ከሸማች ማኅበራትና ከህብረተሰቡ ጋር በትብብር እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በከተማዋ ተፈጥሮ የነበረውን የጸጥታ ችግር ለመፍታት ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር ተከታታይ ውይይቶች መደረጋቸውን ገልጸው በመንደርና በብሎክ ጭምር የህብረተሰብ ውይይቶች ተደርገው ህዝቡን ባሳተፈ መልኩ ሕግና ሥርዓት እንዲከበር ማድረግ ተችሏል ብለዋል።

በትራንስፖርት አገልግሎትና በሌሎችም አገልግሎት ዘርፎች ኅብረተሰቡ የተሻለ አገልግሎት እንዲያገኝ መደረጉንም ተናግረዋል።

ከመንግሥት ሠራተኞች ጋር በአገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ የተደረገው ውይይትም የላቀ ውጤት የተገኘበት መሆኑን ጠቁመዋል።

በመሆኑም አሁን ላይ ደብረ ብርሃን ወደ ቀድሞ ሰላሟ መመለሷንና የመንግሥትና የግል አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ወደ መደበኛ ሥራቸው ተመልሰው የተለመደ ስራቸውን እያከናወኑ እንደሆኑ መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።