ከክልል አደረጃጀት ጋር ተያይዞ የነበረው የህዝብ ጥያቄ ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ እልባት አግኝቷል – ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ

ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ

ነሐሴ 15/2015 (አዲስ ዋልታ) ከክልል አደረጃጀት ጋር ተያይዞ የነበረው የህዝብ ጥያቄ ሰላማዊ፣ ፍትሃዊ እና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ እልባት ማግኘቱን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ገለጹ፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ በወቅታዊ ጉዳይ ላይ በሰጡት መግለጫ ከዚህ ቀደም ህዝቡ በልማት እና በመልካም አስተዳደር ላይ በርካታ ጥያቄዎችን ሲያነሳ እንደነበር አስታውሰው በተለይ ከክልል አደረጃጀት ጋር ተያይዞ የነበረው ጥያቄ እልባት ማግኘቱን አንስተዋል።

ከዚህ ቀደም በልዩ ወረዳነት መዋቅር ስር የነበሩ ህዝቦች በዞን የመደራጀት ፍላጎት እንዳላቸው ስጠይቁ መቆየታቸውን የገለጹት ርዕሰ መስተዳድሩ መንግስት እና መሪው ፓርቲ የህዝቡን የመልማት ጥያቄ በማጤን ምላሽ ለመስጠት ቃል በገባው መሰረት አሁን ላይ ምላሽ ማግኘቱን አብራርተዋል።

አዲስ በተመሰረተው የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ማግስት ላይ የህዝቡ በዞን የመደራጀት ፍላጎቱ እውን መሆኑን ተከትሎ ህዝቡ ለመንግስት እና ለመሪው ፓርቲ አደባባይ በመውጣት ደስታውንና ምስጋናውን ሲገልጽ መቆየቱን በመግለጫቸው ጠቁመዋል።

በዞን የመደራጀት ዋናው አላማ መንግስታዊ አገልግሎቶችን በቅርበት ለህዝቡ ማድረስ ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን አዲስ የተመሰረቱትን የዞን እና የወረዳ መዋቅሮች ፈጥነው ወደ ስራ መግባት እንዳለባቸውና ለዚህም የክልሉ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።
ለህዝብ በቅርበት አገልግሎት መስጠትን መሰረት ባደረገው የክልል፣ የዞን እና የወረዳ መዋቅር በክልሉ ያለውን አቅም በማስተባበር የላቀ የልማት ተጠቃሚነትን ለማሳደግ በትኩረት እንደሚሰራም ርዕሰ መስተዳድሩ ማብራራታቸውን ከክልሉ ኮሙዩኒኬሽን መረጃ አመላክቷል።

ከክልል እስከ ዞን ያለውን አዲስ መዋቅር የህብረተሰቡን የመልማት እና የማደግ ፍላጎት ማሳኪያ አዲስ ምዕራፍ እንደመሆኑ ህብረተሰቡ በሁሉም መስክ መንግስት እና ፓርቲ በሚያደርገው ጥሪ የላቀ ድጋፍና ተሳትፎ እንዲያደርግም ጥሪ አቅርበዋል።