በጋምቤላ ክልል የሰነድ ክምችት ወጪና ፈሰስ ያልተደረገ ከ220 ሚሊየን ብር በላይ ተገኘ

ነሀሴ 01/2013 (ዋልታ) -የጋምቤላ ክልል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት ባካሄደው የፋይናንስ ኦዲት የተሰብሳቢ ሰነድ ክምችት፣ ጉድለት፣ ያልተገባ ወጪና ፈሰስ ያልተደረገ ከ220 ሚሊየን ብር በላይ ማግኘቱን አስታወቀ።

የመስሪያ ቤቱ ዋና ኦዲተር  ኡቻላ ቻም ሰሞኑን ለክልሉ ምክር ቤት ጉባኤ ሪፖርት ሲያቀርቡ እንዳመለከቱት፤ ገንዘቡ የተገኘው በ58 መስሪያ ቤቶች በ2012 በጀት ላይ በ58 መስሪያ ቤቶች በተካሄደ የፋይናንስ ኦዲት ነው።

“በዚህም ከ167 ሚሊዮን ብር በላይ የተሰብሳቢ ሰነድ ክምችት፣ ከሦስት ሚሊዮን 342 ሺህ ብር በላይ የጥሬ ገንዘብ ጉድለት ተገኝቷል” ብለዋል።

በተጨማሪ ከ10 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር በላይ የሠራተኞች የጡረታ መዋጮ ተቆርጦ ፈሰስ አለመደረጉንም ነው ዋና ኦዲተሩ ያስታወቁት።

የመንግስት የግዥ መመሪያን ባልተከተለ መልኩ ከ23 ሚሊዮን ብር በላይ ግዥ ተፈጽሞ መገኘቱንም እንዲሁ።

አቶ ኡቻላ እንዳስረዱት፤ ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ የልማት ድርጅቶችና ሌላ መዋጮ በፔሮል ተቆርጦ ፈሰስ ሳይደረግ ቀርቷል።

ሌሎች በአብላጫና ሰነድ ሳይቆረጥላቸው ወጪ የተደረጉ ሒሳቦችም መገኘታቸውንም አመላክተዋል።

“ከሠራተኞች ለጡረታና ለልማት ቆርጠው ፈሰስ ባላደረጉ መስሪያ ቤቶች ላይ ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤቱ ከክልሉ ገንዘብና ኢኮኖሚ ቢሮ ጋር በመተባበር የእርምት እርምጃ ለመውሰድ እየሰራ ነው” ብለዋል።

የጥሬ ገንዘብ ጉድለት የተገኘባቸውና የመንግስት የፋይናንስ መመሪያን ባልተከተለ መልኩ ወጪ ያደረጉ ተቋማት በተሻሻለው የክልሉ ምክር ቤት አዋጅ መሰረት በህግ እንደሚጠየቁም አስታውቀዋል።

ከምክር ቤቱ አባላት መካከል አቶ ቢተው ዳክ ፤ በየዓመቱ የሚቀርቡት የኦዲት ግኝቶች ላይ የሚሰጠው ግብረ መልስ የሚዘገይበት ሁኔታ መኖሩ አስታውሰው፣ በቀጣይ በዘርፉ ትኩረት ተሰጥቶ መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል።

“ውስን ሃብት ባለበት የሚስተዋለው ተገቢ ያልሆነ የበጀት አጠቃቀም በማህበረሰቡ ላይ ጫናን የሚፈጥር በመሆኑ ጉድለት የታየባቸው ሴክተር መስሪያ ቤቶችን እንደገና በትኩረት ማየት ያስፈልጋል” ያሉት ደግሞ ሌላው የምክር ቤቱ አባል አቶ ታይዶር ቻንባንግ ናችው።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ በበኩላቸው፤ የኦዲት ግኝቱ መልካም አፈፃፀም ቢታይበትም ሀብት በማስመለስ በኩል አፈጻጸሙ ውሱን መሆኑን ተናግረዋል።

የጥሬ ገንዘብ ጉድለት የታየባቸውና የልማት ድርጅቶችን መዋጮ ፈሰስ ባላደረጉ መስሪያ ቤቶች ላይ ፈጣን የማስተካከያ እርምጃ እንዲወሰድ ርዕሰ መስተዳደሩ አመልክተዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።