ሚያዝያ 19/2014 (ዋልታ) በጎንደር በተፈጠረው ግጭት በንጹሃን ሕይወት፣ አካል እና ንብረት ላይ ለደረሰው ጉዳት የአማራ ክልላዊ መንግሥት የተሰማውን ሀዘን ገልጿል፡፡
በድርጊቱ የተሳታፉ ጽንፈኞች ለህግ ለማቅረብ እየሰራ መሆኑን ያስታወቀው የክልሉ መንግሥት ለተጎጂ ቤተሰቦችም መጽናናትን ተመኝቷል፡፡
በጉዳዩ ዙሪያ የአማራ ክልላዊ መንግስት ያወጣው መግለጫ ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ይቀርባል፡-
በጎንደር ከተማ የተከሰተውን ግጭት አስመልክቶ የተሰጠ መግለጫ
የአማራ ሕዝብ በተለያዩ ቦታዎችና ዘርፈ ብዙ በሆኑ ውጫዊ እና ውስጣዊ የማጥቂያ ስልቶች የተወነጨፉበትን ቀስቶች መክቶ ሳይጨርስ በታሪካዊቷና ተቻችሎና ተከባብሮ የመኖር ተምሳሌት በሆነችው ጎንደር ከተማ ውስጥ ሀይማኖትን ሽፋን ያደረገ ግጭት በመቀስቀስ የሕዝቡን አንድነት ለመስበር ጥረት ተደርጓል።
በዛሬው እለት የጎንደር ከተማ ነዋሪ እና የጎንደር ሕዝበ ሙስሊምና ሕዝበ ክርስቲያኑ እንዲሁም የሁሉም አባት የነበሩት ታላቁ ሸኽ ከማል ለጋስ ሥርዓተ ቀብር እየተፈጸመ በነበረበት ሰዓት ከቀብር ቦታው ጋር ድንበርተኛ የሆነው ቤተ ክርስቲያን ላይ ለቀብር የሚሆን ድንጋይ “እናነሳለን የመስጊዱ ክልል ነው፤ አታነሱም የቤተ ክርስቲያኑ ቅጥር ነው” በሚል በተወሰኑ ግለሰቦች መካከል በተጀመረ ግጭት የሰው ህይወት ጠፍቷል፤ የአካል ጉዳትም ደርሷል። የተለያዩ ንብረቶችና ተቋማትን የማጥፋት እንቅስቃሴዎችም ተስተውለዋል።
በተፈጠረው ግጭት በንጹሃን ሕይወት፣ አካል እና ንብረት ላይ በደረሰው ጉዳት የክልሉ መንግሥት ጥልቅ ሀዘን የተሰማው መሆኑን እየገለጽን ለተጎጂ ቤተሰቦችም መጽናናትን እንመኛለን፡፡
የአማራ ክልል መንግሥት በማንኛውንም አይነት የጽንፈኝነት አስተሳሰብ የሚፈጠር የሰላም መደፍረስንም ሆነ በንጹሃን ሕይወት፣ አካልና ሀብት ንብረት ላይ የሚደርስ ጥፋትን የሚሸከምበት ጫንቃ የለውም፡፡ ስለሆነም በጥፋተኞች ላይ አስፈላጊውን ሁሉ ህጋዊ እና ተመጣጣኝ እርምጃም ይወስዳል፡፡
በአሁኑ ሰዓት የክልሉ መንግሥት የተከሰተውን ግጭት ለማብረድ፤ በድርጊቱ የተሳተፉትንና ግጭቱን እያባባሱ ያሉ አካላትንም በቁጥጥር ሥር ለማዋል የክልላችን የጸጥታ ኃይል፣ የሀይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና ሰላም ወዳድ የሆኑት የጎንደር ከተማ ወጣቶች ጋር ተቀናጅቶ ውጤታማ ሥራዎችን በማከናወን ላይ ይገኛል።
በመሆኑም አካባቢውን በማረጋጋት እና ህግና ሥርዓትን በማስከበር ግጭቱን በቁጥጥር ስር ለማዋል ተችሏል፡፡
የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በሰው ሕይወትና ንብረት ላይ የደረሰውን የጉዳት መጠንና ሌሎች አስፈላጊ መረጃዎችን በማሳባሰብ ለሕዝቡ ትክክለኛ መረጃዎችን የመግለጽ፣ የወንጀሉ ተጠርጣሪዎችን በህግ ጥላ ሥር የማዋል፣ ተጎጅዎች ድጋፍ እንዲደረግላቸው የማጣራት ሥራዎችን በማከናወን ለሕዝብ የሚያሳውቅ ይሆናል፡፡
መላው የጎንደር ከተማ ሕዝብ ራሱን፣ አካባቢውን እና ከተማውን በማረጋጋት፣ በመጠበቅና የበኩሉን ሁሉ አስተዋጽኦ በመወጣት መንግሥት አጥፊዎችን በህግ ፊት ለማቅረብ እያከናወነ የሚገኘውን እንቅስቃሴ ከጸጥታ ኃይላችን ጎን በመሆን በተለመደው መንገድ ትብብሩን እንዲያስቀጥል እንጠይቃለን፡፡
የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት
ባሕር ዳር