መጋቢት 9/2014 (ዋልታ) የብልጽግና ፓርቲ በዴሞክራሲያዊና ነጻ ምርጫ ተተኪ አመራሮችን ወደ ኃላፊነት በማምጣት ተራማጅነቱን በተግባር አሳይቷል ሲሉ የፓርቲው ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ተናገሩ፡፡
የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ ምርጫ ሂደት አሳታፊና ትክክለኛ ኅብረ ብሔራዊ ወንድማማችነት የተረጋገጠበት እንደነበርም አንስተዋል፡፡
የብልጽግና ፓርቲ ከሰሞኑን በአዲስ አበባ ባካሄደው የመጀመሪያ ጉባኤው የተለያዩ ውሳኔዎችን አሳልፎ መጠናቀቁ ይታወሳል፡፡
በጉባኤው የተካሄደውን ምርጫ አስመልክቶ ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የፓርቲው ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ጉባኤው በኢትዮጵያ የፖለቲካ ባህል አዲስ ዴሞክራሲያዊ ልምምድ የታየበት ነው ብለዋል፡፡
የብልፅግና ፓርቲ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል የሆኑት ግርማ የሺጥላ በጉባኤው አንዱ ተመልካች ሌላኛው ደግሞ ወሳኝ ሳይሆን ሁሉም የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ያለምንም ገደብ የፈለጉትን አካል መርጠዋል ብለዋል፡፡
የጉባኤው ተሳታፊዎች በብሔርና ክልል አጥር ሳይገደቡ ትክክለኛ ኅብረ ብሔራዊ ወንድማማችነትን በተግባር ማሳየታቸውንም ነው ያነሱት፡፡
ሌላኛዋ የፓርቲው ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል አይናለም ንጉሴ በበኩላቸው በጉባኤው የተካሄደው ምርጫ ፍጹም ዴሞክራሲያዊና ሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎች አርአያ የሚሆን ጭምር ነው ብለዋል፡፡
ጉባኤው አሳታፊ ከመሆኑም ባሻገር ለኢትዮጵያ ሕዝብ በቀጥታ የተላለፈ መሆኑን በማስታወስ ይህም ብልጽግና በኢትዮጵያ ሊያሳካው ለሚፈልገው አሳታፊ የዴሞክራሲ ሥርዓት መሰረት የጣለ ስለመሆኑ ተናግረዋል፡፡